አለሕግAleHig ️
16.2K subscribers
2.87K photos
25 videos
1.87K files
3.58K links
ከጠበቃና የሕግ አማካሪ
አማራጭ የሕግ እውቀትና አገልግሎት
Alternative legal enlightenment & Service
Website: alehig.com
https://linktr.ee/alehig
WhatsApp👉 #+251920666595
Telegram👉 @MikiasMelak
የሕግ ምክርና ድጋፍ፣ የተለያዩ ህጎች፤ አዋጅ፣ ደንብ፣ መመሪያ፣ #የሕግ_መረጃ
Download Telegram
በኮንስትራክሽን ውል ስለ ግንባታ ስራ ርክክብ/Acceptance/
======**=======
#በኮንስትራክሽን ውል ሁለት አይነት የግንባታ ስራ ርክክብ ያለ ሲሆን ይሄውም ግዚያዊ ርክክብ(provisional acceptance) እና የመጨረሻ ርክክብ(final acceptance) የሚያካትት ነው፡፡
#በዚህ ጽሁፍ በዋናነት በኮንስትራክሽን ውል ህግ እውቅና የተሰጣቸውን የርክክብ አይነቶች ምንነትና ተያያዥ ውጤታቸውን አስመልክቶ የህግ ድንጋጌዎችን እና አሁን ላይ በመንግስት ተቋማት እየተሰራበት ያለውን የፒፒኤ 2011 ጀኔራል ኮንዲሽን ድንጋጌዎችን ባካተተ ሁኔታ ለማብራራት ተሞክሯል፡፡
**
#ግዚያዊ ርክክብ/Provisional Acceptance/
#ግዜአዊ ርክክብ በተለይ በኮንስትራክሽን ውል የተመለከቱ የግንባታ ስራዎች ተከናውነው ካበቁ በኋላ ወዲያውኑ ሁለቱ ወገኖች ማለትም አሰሪውና ተቋራጩ ባሉበት በስራው ላይ የሚደረግ የምርመራ ማረጋገጫ ስለመሆኑ የፍትሀብሄር ህግ አንቀጽ 3274(1) ይደነግጋል፡፡ ይሄውም አሰሪው በትክክል የተገነባውን ግንባታ በእጁ አግብቶ መያዙን ጭምር ያረጋግጣል፡፡ ስለዚህ ጊዜአዊ ርክክብ በዋናነት የተሰራውን የግንባታ ስራ አሰሪው መብቱን ጠብቆ በመጀመሪያ የሚረከብበት ሂደት ነው ማለት ነው፡፡በስራው ላይ ምርመራ መደረጉንም የሚያረጋግጥ ነው፡፡
#ፒፒኤ 2011 ክሎስ 84.1 ላይ የስራ ምርመራ/verification and test/ በመሀንዲሱ ተቋራጭ ባለበት ሊደረግ እንደሚገባ በመርህ ደረጃ ተቀምጧል፡፡ሆኖም ግን ተቋራጩ ምርመራው ከሚካሄድበት እለት ከ30 ቀን በፊት በተገቢ ሁኔታ እንዲያውቀው ተደርጐ በምርመራው እለት ያልተገኘ እንደሆነ የስራ ምርመራው ተቋራጩ በሌለበት ሊካሄድ እንደሚችል ይፈቅዳል፡፡
#እንግዲህ መሀንዲሱ ስራውን ከመረመረ በኋላ ያላመነበትን የስራ ክፍል ፈርሶ እንደገና እንዲሰራ ወይም እንዲጠገን ተደርጐ የጥራት ደረጃውን ባሟላ ሁኔታ እንዲከናወን ለማዘዝ እንደሚችል ፒፒኤ ክሎስ 85 ይፈቅድለታል፡፡
#በዚህም መሰረት ግንባታው የስራ ምርመራውን ካለፈ አሰሪው ግንባታውን የሚረከበው ይሆናል ማለት ነው፡፡ስለዚሁም የጊዜአዊ ርክክብ ሰርተፍኬት ለተቋራጩ የሚሰጠው ይሆናል፡፡በመሰረቱ ተቋራጩ የጊዜአዊ ርክክብ ሰርተፍኬት እንዲሰጠው መጠየቅ ያለበት ስራው ሊጠናቀቅ ይችላል ብሎ ከሚያስብበት ከ15 ቀን በፊት መሆን ይኖርበታል፡፡ከዚያም መሀንዲሱ ጥያቄው በደረሰው በ30 ቀን ውስጥ የስራ ምርመራውን አጠናቆ ሰርተፍኬቱን መስጠት ወይም ጥያቄውን ውድቅ ማድረግ ይኖርበታል፡፡መሀንዲሱ ሰርተፍኬቱን ሳይሰጥ ወይም ጥያቄውን ውድቅ ሳያደርግ 30 ቀኑ ያለፈ እንደሆነ ለተቋራጩ የጊዜአዊ ርክክብ ሰርተፍኬት እንደተሰጠው ግምት እንደሚወሰድ ፒፒኤ ክሎስ 87 ያስቀምጣል፡፡
#ሌላው ተቋራጩ በስራው ላይ ያደረገው መሻሻል/መለወጥ ቢኖር እንኳ በዝምታ ግዜአዊ ርክክብ ከተደረገ መሻሻሉ ተቀባይነት እንዳገኘ የህግ ግምት እንደሚያስወስድ የፍትሀብሄር ህግ አንቀጽ 3275(2) ይደነግጋል፡፡እዚህ ላይ ተቋራጩ በተሰጠው ዲዛይን መሰረት የመስራት ግዴታ ያለበት መሆኑ ይታዎቅ፡፡ ስለዚህ የህግ ግምቱ እሳቤ ተቋራጩ ከዲዛይኑ በመውጣት አሻሽሎ የሰራው ስራ ኖሮ በግዜአዊ ርክክብ ወቅት በዝምታ አሰሪው ካለፈው እንደተቀበለው ይቆጠራል ነው፡፡
#እንዲሁም ግዜአዊ ርክክብ መደረጉ የመድህንነት ጊዜው(warranty period) መጀመሩን እንደሚያመለክት የፍትሀብሄር ህግ አንቀጽ 3275(3) ይደነግጋል፡፡
**
#የመድህንነት ጊዜ(warranty period/Defects Liability period)
#የመድህንነት ጊዜ(warranty period) የሚባለው ከጊዜአዊ ርክክብ እስከ መጨረሻ ርክክብ ያለው ጊዜ ሲሆን አሰሪው ግንባታው በተቋራጩ በደህና ሁኔታ ስለመሰራቱ ለመመርመርና ለማረጋገጥ የሚያስችለው ጊዜ ነው፡፡የጊዜው ርዝማኔም በውላቸው ላይ የሚወሰን ስለመሆኑ የፍትሀብሄር ህግ አንቀጽ 3277 ይደነግጋል፡፡ ሆኖም በውሉ ላይ የመድህንነት ጊዜው ርዝማኔ ያልተጠቀሰ እንደሆነ ከጊዜአዊ ርክክብ ቀን ጀምሮ 365 ቀን ስለመሆኑ የፒፒኤ ክሎስ 88.7 ያስቀምጣል፡፡
#ተቋራጩ በዚሁ በመድህንነት ጊዜ በተለይ የተበላሹ ስራዎችን እንዲያድሳቸው በአሰሪው በታዘዘ ጊዜ የማስተካከል ግዴታ እንዳለበት የፍትሀብሄር ህግ አንቀጽ 3278 ይደነግጋል፡፡ ለዚህም ለጥገና ወጭ ሲባል ከተቋራጩ ክፍያ ላይ ሪቴንሽን ገንዘብ(retention money or bond) 5% እየተቀነሰ በአሰሪው ይያዛል፡፡
#በመድህንነት ጊዜ ውስጥ የተለዩ ብልሽት ያለባቸው ስራዎችን እንዲያስተካክል ተቋራጩ ተጠይቆ በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ያላስተካከለ እንደሆነ አሰሪው የማስተካከያ ስራውን በተቋራጩ ወጭ በራሱ ወይም ሌላ ቀጥሮ ሊያሰራው ወይም ውሉን ሊያቋርጥ ስለመቻሉ ፒፒኤ ክሎስ 88.3 ለአሰሪው መብት ይሰጠዋል፡፡
**
#ከፊል ርክክብ/Partial Acceptance/
-በፒፒኤ ክሎስ 86 ላይ የግንባታ ስራው በከፊል እርክክብ የሚደረግበትንም አማራጭ ያስቀምጣል፡፡ይህ ማለት የተወሰነውን የስራ ክፍል(part of the work) ከአጠቃላይ ውሉ ጊዜ በፊት ለማስረከብ በውል ላይ ከተቀመጠ ተቋራጩ የተወሰነውን የስራ ክፍል ከአጠቃላይ የውሉ ጊዜ በፊት ለማስረከብ ይገደዳል ማለት ነው፡፡በዚህም በአንድ ውል ውስጥ በተለያየ ጊዜ ጊዜአዊ ርክክብ ሊደረግ የሚችልበትን ሁኔታ ይፈጥራል ማለት ነው፡፡
**
#የመረሻ ርክክብ/Final Acceptance/
#የመጨረሻ ርክክብ/Final Acceptance/ በተለይ የመድህንነት ጊዜ ካለቀ በኋላ እና ተቋራጩ ጠቅላላ ግዴታዎቹን በደህና ሁኔታ የፈጸመ መሆኑን አሰሪው ሲያረጋግጥ ግንባታውን ሙሉ በሙሉ በእጁ የሚያደርግበት(definitively appropriate) ስለመሆኑ የፍትሀብሄር ህግ አንቀጽ 3279 ይደነግጋል፡፡
#የመጨረሻ ርክክብ አሰሪውና ተቋራጩ ባሉበት በጽሁፍ መደረግ እንዳለበት በአስገዳጅ ሁኔታ በፍትሀብሄር ህግ አንቀጽ 3279(2) ላይ ተደንግጓል፡፡ሆኖም ጊዜአዊ ርክክብ/ Provisional Acceptance/ በሚመለከት ግን በጽሁፍ መደረግ እንዳለበት የሚያስገድድ ግልጽ ህግ የለም፡፡ስለዚህ ስራው ተጠናቆ አሰሪው ግንባታውን በእጁ ካስገባ ጊዜአዊ ርክክብ መደረጉን የሚያስገነዝብ ይሆናል ማለት ነው፡፡በእርግጥ በጽሁፍ መደረጉ ይመከራል፡፡
#በፍትሀብሄር ህግ አንቀጽ 3282 ላይ እንደተቀመጠው ከመጨረሻ ርክክብ በኋላ ተቋራጩ እስከ 10 አመት ድረስ ስለስራው አሰራር ጉድለት ተቋራጩ ሀላፊነት አለበት፣መድህን ሆኖ ይቀጥላል፡፡በመጨረሻ ርክክብ ወቅት የሚታዩ ለነበሩ ጉድለቶች(apparent defect) ግን ተቋራጩ ሀላፊነት የለበትም፡፡ሀላፊነቱ የሚመለከተው ግንባታው በውሉ የተመለከተውን የታለመለትን ጥቅም እንዳይሰጥ የሚያደርጉ ወይም አጠቃቀሙን በጣም ውድ የሚያደርጉና አክሳሪ የሚያደርጉ ጉድለቶችን ነው፡፡
#henoktayelawoffice
👍4
ከውል ውጪ ስለሚደርስ ጉዳት ካሳ ማወቅ ያለብዎት ነገር
ሰዎች በተለያዩ ምክንያቶች ጉዳት ሊደርስባቸው ይችላል።

እነዚህ ጉዳቶች ከወንጀል ድርጊት፣ ከውል ጥሰት ወይም ከውል ውጪ ከሚመጣ ኃላፊነት ሊነሱ ይችላሉ። የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የህግ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ከፍተኛ የህግ ባለሙያ የሆኑት አቶ ደመቀ ይብሬ እንደሚሉት፣ ከውል ውጪ በሚደርስ ጉዳት ህግ ዋነኛ ዓላማ ጉዳት ያደረሰውን አካል በመለየት ተጎጂው ተገቢውን ካሳ እንዲያገኝ ማስቻልና ሌሎችም ከዚህ እንዲማሩ ማድረግ ነው።

#ጉዳት ምንድን ነው?
የፍትሐ ብሔር ህጉ ለ"ጉዳት" የሚለው ቃል ቀጥተኛ ትርጉም ባይሰጥም፣ ከህጉ አጠቃላይ ይዘት በመነሳት በሰው ጥቅም፣ አካል ወይም ህይወት ላይ የሚደርስ ጉድለት መሆኑን መረዳት ይቻላል።

#ለካሳ ክፍያ መሟላት ያለባቸው ነገሮች
ከውል ውጪ ባለው የኃላፊነት ህግ መሰረት ካሳ ለማስከፈል፣ ተጎጂው ጉዳት እንደደረሰበት እና ጉዳቱም የደረሰው ኃላፊነት አለበት በተባለው ሰው ድርጊት ወይም እሱ ኃላፊነት በሚወስድባቸው ድርጊቶች መሆኑን ማረጋገጥ አለበት።
የኃላፊነት ምንጮች
ከፍተኛ የህግ ባለሙያው አቶ ደመቀ እንደሚጠቅሱት፣ ከውል ውጪ የሚደርስ ኃላፊነት ህግ መሰረት (የፍትሐ ብሔር ህግ ቁጥር 2027) ሶስት አይነት የኃላፊነት ምንጮች አሉ፦
#በጥፋት ላይ የተመሰረተ ኃላፊነት
#ጥፋት ሳይኖር የሚመጣ ኃላፊነት
#ሌላ ሰው ለሚያደርሰው ጉዳት የሚኖር ኃላፊነት
የጉዳት ዓይነቶች
የህግ ባለሙያው እንዳብራሩት፣ የተለያዩ የጉዳት ዓይነቶች አሉ።
1. ግልጽ የሆኑ ጉዳቶች
እነዚህ ጉዳቶች የተጎጂውን ንብረት ወይም ገንዘብ ነክ ጥቅም በቀጥታ የሚነኩ ናቸው። ይህ የጉዳት አይነት ቀጥታ ንብረት ላይ የሚደርስ ጉዳትን ወይም በአካልና በህይወት ላይ የሚደርስ ጉዳትን ያጠቃልላል።
ግልጽ የሆኑ ጉዳቶች አሁን የደረሱ ወይም ወደፊት የሚደርሱ ሊሆኑ ይችላሉ።

#አሁን የደረሱ ጉዳቶች: የፍትሐ ብሔር ህግ ቁጥር 2090 እንደሚያመለክተው፣ እነዚህ በአሁኑ ጊዜ በእርግጠኝነት የደረሱና በግልጽ የሚታወቁ ጉዳቶች ሲሆኑ፣ ከደረሱበት ጊዜ ጀምሮ የጉዳትና የካሳ መጠኑ በፍርድ ቤት እስከሚወሰንበት ጊዜ ድረስ ያለውን ይመለከታል።

#ወደፊት የሚደርሱ ጉዳቶች: የፍትሐ ብሔር ህግ ቁጥር 2092 እንደሚያስረዳው፣ በደረሰው ጉዳትና በካሳ ተመኑ ላይ ፍርድ ከተሰጠ በኋላ የማይቆሙና የሚቀጥሉ የጉዳት ዓይነቶች ናቸው።
2. የህሊና ጉዳት
ይህ የጉዳት አይነት የተጎጂውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም የማይጎዳ ሆኖም በስሜት፣ በሀዘን ወይም በሀፍረት መልክ የሚገለጽ ሞራላዊ ጉዳት ነው።
የጉዳት ካሳ ስሌት
ጉዳትን ተከትሎ የሚመጣው ካሳ፣ ለጉዳት ለደረሰበት ሰው የጉዳት መጠኑ ተሰልቶ በዛ ልክ የሚሰጠው ጥቅም ነው። የፍትሐ ብሔር ህግ ቁጥር 2090(1) እና 2091 ይህንን ያብራራል።
ለተጎጂው የሚገባውን ካሳ ለማስላት፣ የተጎጂውን የስራ ሁኔታ ማወቅ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው። ጉዳት የደረሰበት ሰው ተቀጥሮ የሚሰራ፣ የራሱን ስራ እየሰራ የሚኖር ወይም ስራ በመስራት ላይ ያልነበረ ሊሆን ይችላል።
1. ተቀጥሮ ለሚሰራ ሰው የሚሰጥ ካሳ
ጉዳቱ ከስራው ጋር የተገናኘ ከሆነ፣ የክርክሩ ሂደትና የካሳ አሰላል ስርዓቱ በአሰሪና ሰራተኛ ህግ (ቁጥር 1064/2010 እና 1156/2011) መሰረት ይመራል። ከስራው ጋር የማይገናኝ ከሆነ ግን በከውል ውጪ ኃላፊነት የህግ ድንጋጌዎች ይመራል።
#ጊዜያዊ ጉዳት: ጉዳቱ ጊዜያዊ ከሆነ፣ ስራ እስከሚጀምር ድረስ ሊያገኝ ይችል የነበረውን ያክል ካሳ ያገኛል።
#ከፊል ቋሚ ጉዳት: መስራት ባላስቻለው መጠን ልክ ይሰላል።
#ቋሚ ጉዳት: እስከ ጡረታ ጊዜው ድረስ ተሰልቶ ይሰጠዋል።
የአካል ጉዳት ሲደርስ፣ የወደፊት ጉዳት ካሳ ስሌት ላይ የደረሰውን የጉዳት መጠን፣ የሰራተኛውን የገቢ መጠን እና ተጎጂው ጡረታ ለመውጣት የቀረውን ጊዜ በደንብ ማጤን ያስፈልጋል።
2. የራሱን ስራ ለሚሰራ ሰው የሚሰጥ ካሳ
የራሱን ስራ እየሰራ ለሚተዳደር ሰው ካሳውን ለማስላት ገቢውን ለማወቅ አስቸጋሪ ሊሆን ቢችልም፣ የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም ወርሃዊ ወይም አመታዊ አማካይ ገቢውን በመመልከት ያጣውን ወይም ሊያጣ የሚችለውን ጥቅም በማስላት ካሳውን መተመን ይቻላል።
3. ስራ አጥ ለነበረ ሰው የሚሰጥ ካሳ
በህመም፣ ለመስራት ባለመፈለግ፣ የሚመጥነውን ስራ በማጣት ወይም በጠቅላላው ስራ አጥ በመሆን ስራ እየሰሩ ያልነበሩ ሰዎች ላይ ጉዳት ቢደርስባቸው የገቢውን መጠን ማወቅ ስለሚያስቸግር ካሳውን ማስላት ይከብዳል። በዚህ ጊዜ ዳኞች በፍትሃዊነት (በርትዕ) ካሳውን ለማስላት ይገደዳሉ።
4. በሞት ምክንያት የሚሰጥ ካሳ
በአደጋ ምክንያት ሞት ሲያጋጥም፣ ካሳ የመጠየቅ መብት ያለው ማነው የሚለው ወሳኝ ነው። የፍትሐ ብሔር ህግ ቁጥር 2095 መሰረት የሟች ባል/ሚስት፣ ወላጆች እና ተወላጆች ካሳ መጠየቅ ይችላሉ። ለእነዚህ ሰዎች የሚከፈለው ካሳ ቀለብ ስለሆነ፣ በቤተሰብ ህጉ መሰረት ቀለብ ጠያቂ ሊያሟላቸው የሚገቡ መስፈርቶችን ማሟላትና ማስረዳት ይጠበቅባቸዋል።
5. ለህሊና ጉዳት የሚሰጥ ካሳ
የህሊና ጉዳት የሰው ልጅ የውስጥ ስሜት ጉዳት በመሆኑ ካሳውን በገንዘብ መለካት አስቸጋሪ ነው። ሆኖም የህሊና ጉዳት ሲያጋጥም የገንዘብ ካሳ እንደሚከፈል በፍትሐ ብሔር ህግ ቁጥር 2105(1) ተቀምጧል።
የህሊና ጉዳት ካሳ የሚከፈለው በልዩ ሁኔታ በህግ ለተመለከቱ ጉዳቶች ብቻ እንጂ ሁልጊዜም ካሳ እንደማያስከፍል የፍትሐ ብሔር ህግ ቁጥር 2105(2) ይደነግጋል። የህሊና ጉዳት ካሳ የሚወሰነው ርትዕን መሰረት አድርጎ ሲሆን፣ የፍትሐ ብሔር ህግ ቁጥር 2106-2115 ይህንን ያብራራል። የህሊና ጉዳት ካሳ 1,000 ብር መብለጥ እንደሌለበት የፍትሐ ብሔር ህግ ቁጥር 2116(3) ያስቀምጣል።
የካሳ አከፋፈል ስርዓት
ጉዳት መድረሱ፣ ለጉዳቱ ማን ኃላፊነት እንደሚወስድና የካሳ ክፍያው መጠን ከተለየ በኋላ መወሰን ያለበት ሌላ ወሳኝ ጉዳይ የካሳ አከፋፈል ስርዓቱ ነው። የህግ ባለሙያው እንዳሉት፣ ሁለት አይነት የካሳ አከፋፈል ስርዓቶች አሉ፦
1. የቁርጥ ክፍያ
ይህ የካሳ ክፍያ የተወሰነበትን መጠን በአንድ ጊዜ ለባለመብቱ በመክፈል የሚፈጸም ነው። ይህ ዘዴ በብዙ ሀገራት የሚተገበርና መርህም ነው።
2. በየጊዜው የሚደረግ ክፍያ
መርሁ የጉዳት ካሳን በቁርጥ መክፈል ቢሆንም፣ በልዩ ሁኔታ ግን በየጊዜው እንዲከፈል ተደርጎ መወሰን እንደሚቻል በህጉ ተቀምጧል። ካሳን በየጊዜው እንዲከፈል ለመወሰን፣ የካሳው ባህሪ፣ የአካባቢ ሁኔታዎች እና የካሳ ከፋዩ ማረጋገጫ መስጠት ያለባቸው ነጥቦች ናቸው።
#Mikias_Melak
በማናቸውም ፍርድ ቤት ጠበቃ እና የሕግ አማካሪ
Alternative legal enlightenment & Service
https://linktr.ee/alehig
WhatsApp👉 #+251920666595
Telegram👉 @MikiasMelak
#የሕግ_መረጃ https://t.me/AleHig
#የሕግ_እውቀት alehig.com
#AleHig #አለሕግ #አለሕግ #ህግ
9