አለሕግAleHig ️
16.2K subscribers
2.87K photos
25 videos
1.87K files
3.58K links
ከጠበቃና የሕግ አማካሪ
አማራጭ የሕግ እውቀትና አገልግሎት
Alternative legal enlightenment & Service
Website: alehig.com
https://linktr.ee/alehig
WhatsApp👉 #+251920666595
Telegram👉 @MikiasMelak
የሕግ ምክርና ድጋፍ፣ የተለያዩ ህጎች፤ አዋጅ፣ ደንብ፣ መመሪያ፣ #የሕግ_መረጃ
Download Telegram
ℹ️ #በጥፋት_ከሥራ_የሚያሰናብቱ_በቂ_ምክንያቶች ⤵️

1/ የሥራ ሰዓት አለማክበር

የሥራ ሰዓት አለማክበር ሲባል በሥራ መግቢያ ሰዓት ማርፈድ፤ ከሥራ መውጪያ ሰዓት ቀደም ብሎ መውጣትና በሥራ ሰዓት የሥራ ቦታን ጥሎ መሄድን ያጠቃልላል፡፡ በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ 1156/2011 አንቀጽ 27(1) ሀ መሠረት 👉በሥራ ውሉ ከተዘረዘሩት ምክንያቶች ውጭ ሠራተኛው የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ እየተሰጠው በስድስት ወር ውስጥ በጠቅላላው ለስምንት ጊዜ የስራ ሰዓት ያላከበረ ከሆነ የሥራ ውልን ለማቋረጥ አሠሪው መብት ይኖረዋል ::

2/ ከሥራ መቅረት

በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ 1156/2011 ከተመለከቱ እረፍቶች እና ልዩ ልዩ ፈቃዶች ውጭ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ እየተሰጠው #በስድስት ወር ውስጥ ለአምስት ቀናት ከስራ
መቅረት፤ የሥራ ውልን ያለማስጠንቀቂያ እንሚያቋርጥ በአዋጁ አንቀጽ 27(1) ለ ተመልክቷል፡፡

3/ ማታለል ወይም ማጭበርበር

የአሠሪና ሠራተኛ ግንኙነት በዋነኛነት በመተማመን ላይ የተመሰረተ እንደመሆኑ ሠራተኛው ታማኝ ሆኖ የመገኘት ግዴታውን ወደ ጎን በመተው በአሠሪው ላይ የሚፈጽማቸው የማታለልና የማጭበርበር ድርጊቶች የሥራ ውሉን ለማቋረጥ በቂ ተደርገው የመወሰዳቸው አግባብነት የሚያከራክር አይሆንም፡፡ ይሁን እንጂ ማታለል ወይም ማጭበርበር በመፈጸሙ ብቻ የስንብት እርምጃ መውሰድ ተገቢ አይደለም፡፡ ህጉ ማታለል ወይም ማጭበርበር ሲኖር የሥራ ውል የሚቋረጥባቸውን ሁኔታዎች በግልጽ ያስቀመጠ እንደመሆኑ በቅድሚያ ሁኔታዎቹ ተሟልተው ሊገኙ ይገባል፡፡

በአዋጁ አንቀጽ 27(1) ሐ እንደተመለከተው በሥራው ላይ የማታለል ወይም የማጭበርበር ተግባር መፈጸም የሥራ ውልን ያለማስጠንቀቂያ ለማቋረጥ አንደኛው በቂ ምክንያት ነው፡፡

4/ በአሠሪው ንብረት ወይም ገንዘብ አላአግባብ መጠቀም

ሠራተኛው ለሥራው የተሰጡትን መሣሪዎችና ዕቃዎች ሁሉ በጥንቃቄ የመጠበቅ የህግ ግዴታ ተጥሎበታል፡፡ ስለሆነም ጥሬ ገንዘብን ጨምሮ ሥራውን እንዲያከናውን የሚረዱት ሌሎች ከአሠሪው የተረከባቸውን ንብረቶች በራሱ ወይም በሌላ ሰው ጉዳት እንዳይደርስባቸው ብሎም ለብክነትና ለብልሽት እንዳይዳረጉ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እና ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ለሚሰራው ሥራ ዓላማ ካልሆነ በስተቀር የግሉን ወይም የሌላ 3ኛ ወገን ብልጽግና በመሻት ሊጠቀምባቸው አይገባም፡፡ ግዴታው የታማኝነቱ ቁልፍ መገለጫ ነው፡፡ የአሠሪና ሠራተኛ ግንኙነት በመተማመን ላይ የተመሰረተ እንደመሆኑ በማናቸውም የአሠሪውን ጥቅም በሚመለከቱ ጉዳዮች ሠራተኛው ሁልጊዜ ታማኝ ሆኖ መገኘት አለበት፡፡

በመሆኑም በአዋጁ አንቀጽ 27(1) ሐ መሠረት በአሠሪው ንብረት ወይም ገንዘብ አላአግባብ መጠቀም የሥራ ውልን ያለማስጠንቀቂያ ለማቋረጥ በቂ ምክንያት ነው፡፡

5/ ጠብ አጫሪነት ወይም አምባጓሮ

በሥራ ቦታ ላይ የሚከሰት ጠብ እና አምባጓሮ ሰላማዊ የሥራ አካባቢን የሚያውክና ስርዓት አልበኝነትን የሚያነግስ በመሆኑ በአጭሩ ካልተቀጨ የአሠሪውን ምርታማነት በእጅጉ ይጎዳል፡፡ አንድ ሠራተኛ ተመድቦ የሚሰራበት ሥራ ከሌላ ሠራተኛ ሥራ ጋር በእጅጉ የተሳሰረ ነው፡፡ ጠብና አምባጓሮ ሲፈጠር ሥራ በቅንጅትና በመግባባት አይሰራም፡፡ ከአሠሪው ድርጅት ምርትና አገልግሎት የሚፈልጉ ደንበኞችም ያርቃል፡፡ የአንቀጽ 27(1) ረ አይነተኛ አላማ በሥራ ቦታ ሰላም እንዲሰፍን በማድረግ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ነው፡፡ በመሆኑም በአዋጁ አንቀጽ 27(1) ረ መሠረት በስራ ቦታ ጠብ አጫሪ መሆን ወይም አምባጓሮ መፍጠር የሥራ ውልን ያለማስጠንቀቂያ ለማቋረጥ በቂ ምክንያት ነው፡፡

6/ በአሠሪው ንብረት ላይ ጉዳት ማድረስ

በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ አንቀጽ 27(1) ሸ አነጋገር ሠራተኛው ከሥራ የሚሰናበተው ሆነ ብሎ ወይም በከባድ ቸልተኝነት ጉዳት ሲያደርስና ጉዳቱም የደረሰው በአሠሪው ንብረት ወይም ከድርጅቱ ሥራ ጋር በቀጥታ ግንኙነት ባለው ማናቸውም ንብረት ላይ መሆኑ ሲረጋገጥ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር አራት የጥፋቱ ማቋቋሚያዎች አንድ ላይ ተሟልተው መገኘት እንዳለባቸው እንረዳለን፡፡ ይኸውም፤

#አንደኛ ጉዳት ደረሰበት የተባለው ነገር “ንብረት” መሆን አለበት፡፡ በሌላ አነጋገር ህጉ ለንብረት የሰጠውን ፍቺ ማሟላት ይኖርበታል፡፡

#ሁለተኛ ንብረቱ የአሠሪው ወይም ከድርጅቱ ሥራ ጋር በቀጥታ ግንኙነት ያለው ንብረት ሊሆን ይገባል፡፡

#ሶስተኛ አሠሪው በንብረቱ ወይም ከድርጅቱ ሥራ ጋር በቀጥታ ግንኙነት ባለው ንብረት ላይ የደረሰ ጉዳት ስለመኖሩ ብሎም በጉዳቱና በድርጊቱ መካከል የምክንያትና ውጤት ግንኙነት ስለመኖሩ ማስረዳት ይኖርበታል፡፡ የምክንያትና ውጤት ግንኙነት ሲባል ሠራተኛው ማድረግ የሌለበትን በማድረጉ ወይም ማድረግ ያለበትን ባለማድረጉ ምክንያት ጉዳት መከሰቱን ለማመልከት ነው፡፡

#አራተኛ ሠራተኛው ጉዳቱን ያደረሰው ሆነ ብሎ ወይም በከባድ ቸልተኝነት ስለመሆኑ መረጋገጥ ይኖርበታል፡፡

በመሆኑም በአዋጁ አንቀጽ 27(1) ሸ መሠረት በአሠሪው ንብረት ወይም ከድርጅቱ
ሥራ ጋር በቀጥታ ግንኙነት ባለው ማናቸውም ንብረት ላይ ሆነ ብሎ ወይም በከባድ ቸልተኝነት ጉዳት ማድረስ የሥራ ውልን ያለማስጠንቀቂያ ለማቋረጥ በቂ ምክንያት ነው፡፡

7/ የወንጀል ጥፋተኝነትና እስራት

የወንጀል ጥፋተኝነት የሥራ ውልን ለማቋረጥ በራሱ በቂ ምክንያት ባይሆንም በውጤቱ ሠራተኛውን ለያዘው ሥራ ብቁ የማያደርገው ከሆነ [አንቀጽ 27(1) ሰ] ወይም የእስራቱ ጊዜ ከሰላሳ ቀን ከበለጠ [አንቀጽ 27(1) በ] ህጋዊ የስራ ውል ማቋረጫ ምክንያት ይሆናል፡፡ በአንቀጽ 27(1) ሰ ከጥፋተኝነት ባለፈ የእስራት ፍርድ እንዲኖር የግድ አይልም፡፡ ሠራተኛው ቅጣቱ ቢገደብለትም ብሎም በገንዘብ መቀጮ ብቻ ቢቀጣም ጥፋተኛ የተባለበት ወንጀል ብቃቱን የሚያሳጣው ከሆነ ከአሠሪው ጋር ያለው ግንኙነት ይቋረጣል፡፡

8/ የሥራ ውጤት መቀነስ (መለገም)

ሠራተኛው መውጫና መግቢያ ሰዓት አክብሮ በሥራ ቦታ መገኘቱ ብቻውን የመስራት ግዴታውን እየተወጣ ነው አያስብልም፡፡ ግዴታውን ሲወጣ መላ ጉልበቱን፤ ችሎታውንና ዕውቀቱን በመጠቀም የተመደበበትን ሥራ ጥንካሬና ትጋት በተሞላበት መልኩ በማከናወን ውጤት ማምጣት አለበት፡፡ በዳተኝነት፤ ልግመኝነትና ንዝህላልነት ሥራን መበደል ካለማስጠንቀቂያ የሚያሰናብት ጥፋት ነው፡፡ የሥራ ችሎታ መቀነስ በአንቀጽ 28(1) ሀ በማስጠንቀቂያ የሥራ ውልን የሚያቋርጥ በቂ ምክንያት ሲሆን ይህም ተፈጥሯዊ በሆነ ምክንያት ሊከሰት ስለሚችል በአንቀጽ 27(1) ሠ ጥፋት ከሆነው የሥራ ውጤት መቀነስ እንዲለይ ተደርጓል፡፡ አንቀጽ 27(1) ሠ ተፈጻሚ የሚሆነው ሠራተኛው የመስራት ችሎታውና ብቃቱ እያለው ሆነ ብሎ ወይም በቸልተኝነት ከሚጠበቅበት በታች በመስራት ሥራ ሲበድል ማለትም ሲያለግም ነው፡፡

የሕግ አማካሪና ጠበቃ ሳሙኤል ግርማ
https://t.me/YehigGuday
👍11🔥3😁1
ከውል ውጪ ስለሚደርስ ጉዳት ካሳ ማወቅ ያለብዎት ነገር
ሰዎች በተለያዩ ምክንያቶች ጉዳት ሊደርስባቸው ይችላል።

እነዚህ ጉዳቶች ከወንጀል ድርጊት፣ ከውል ጥሰት ወይም ከውል ውጪ ከሚመጣ ኃላፊነት ሊነሱ ይችላሉ። የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የህግ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ከፍተኛ የህግ ባለሙያ የሆኑት አቶ ደመቀ ይብሬ እንደሚሉት፣ ከውል ውጪ በሚደርስ ጉዳት ህግ ዋነኛ ዓላማ ጉዳት ያደረሰውን አካል በመለየት ተጎጂው ተገቢውን ካሳ እንዲያገኝ ማስቻልና ሌሎችም ከዚህ እንዲማሩ ማድረግ ነው።

#ጉዳት ምንድን ነው?
የፍትሐ ብሔር ህጉ ለ"ጉዳት" የሚለው ቃል ቀጥተኛ ትርጉም ባይሰጥም፣ ከህጉ አጠቃላይ ይዘት በመነሳት በሰው ጥቅም፣ አካል ወይም ህይወት ላይ የሚደርስ ጉድለት መሆኑን መረዳት ይቻላል።

#ለካሳ ክፍያ መሟላት ያለባቸው ነገሮች
ከውል ውጪ ባለው የኃላፊነት ህግ መሰረት ካሳ ለማስከፈል፣ ተጎጂው ጉዳት እንደደረሰበት እና ጉዳቱም የደረሰው ኃላፊነት አለበት በተባለው ሰው ድርጊት ወይም እሱ ኃላፊነት በሚወስድባቸው ድርጊቶች መሆኑን ማረጋገጥ አለበት።
የኃላፊነት ምንጮች
ከፍተኛ የህግ ባለሙያው አቶ ደመቀ እንደሚጠቅሱት፣ ከውል ውጪ የሚደርስ ኃላፊነት ህግ መሰረት (የፍትሐ ብሔር ህግ ቁጥር 2027) ሶስት አይነት የኃላፊነት ምንጮች አሉ፦
#በጥፋት ላይ የተመሰረተ ኃላፊነት
#ጥፋት ሳይኖር የሚመጣ ኃላፊነት
#ሌላ ሰው ለሚያደርሰው ጉዳት የሚኖር ኃላፊነት
የጉዳት ዓይነቶች
የህግ ባለሙያው እንዳብራሩት፣ የተለያዩ የጉዳት ዓይነቶች አሉ።
1. ግልጽ የሆኑ ጉዳቶች
እነዚህ ጉዳቶች የተጎጂውን ንብረት ወይም ገንዘብ ነክ ጥቅም በቀጥታ የሚነኩ ናቸው። ይህ የጉዳት አይነት ቀጥታ ንብረት ላይ የሚደርስ ጉዳትን ወይም በአካልና በህይወት ላይ የሚደርስ ጉዳትን ያጠቃልላል።
ግልጽ የሆኑ ጉዳቶች አሁን የደረሱ ወይም ወደፊት የሚደርሱ ሊሆኑ ይችላሉ።

#አሁን የደረሱ ጉዳቶች: የፍትሐ ብሔር ህግ ቁጥር 2090 እንደሚያመለክተው፣ እነዚህ በአሁኑ ጊዜ በእርግጠኝነት የደረሱና በግልጽ የሚታወቁ ጉዳቶች ሲሆኑ፣ ከደረሱበት ጊዜ ጀምሮ የጉዳትና የካሳ መጠኑ በፍርድ ቤት እስከሚወሰንበት ጊዜ ድረስ ያለውን ይመለከታል።

#ወደፊት የሚደርሱ ጉዳቶች: የፍትሐ ብሔር ህግ ቁጥር 2092 እንደሚያስረዳው፣ በደረሰው ጉዳትና በካሳ ተመኑ ላይ ፍርድ ከተሰጠ በኋላ የማይቆሙና የሚቀጥሉ የጉዳት ዓይነቶች ናቸው።
2. የህሊና ጉዳት
ይህ የጉዳት አይነት የተጎጂውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም የማይጎዳ ሆኖም በስሜት፣ በሀዘን ወይም በሀፍረት መልክ የሚገለጽ ሞራላዊ ጉዳት ነው።
የጉዳት ካሳ ስሌት
ጉዳትን ተከትሎ የሚመጣው ካሳ፣ ለጉዳት ለደረሰበት ሰው የጉዳት መጠኑ ተሰልቶ በዛ ልክ የሚሰጠው ጥቅም ነው። የፍትሐ ብሔር ህግ ቁጥር 2090(1) እና 2091 ይህንን ያብራራል።
ለተጎጂው የሚገባውን ካሳ ለማስላት፣ የተጎጂውን የስራ ሁኔታ ማወቅ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው። ጉዳት የደረሰበት ሰው ተቀጥሮ የሚሰራ፣ የራሱን ስራ እየሰራ የሚኖር ወይም ስራ በመስራት ላይ ያልነበረ ሊሆን ይችላል።
1. ተቀጥሮ ለሚሰራ ሰው የሚሰጥ ካሳ
ጉዳቱ ከስራው ጋር የተገናኘ ከሆነ፣ የክርክሩ ሂደትና የካሳ አሰላል ስርዓቱ በአሰሪና ሰራተኛ ህግ (ቁጥር 1064/2010 እና 1156/2011) መሰረት ይመራል። ከስራው ጋር የማይገናኝ ከሆነ ግን በከውል ውጪ ኃላፊነት የህግ ድንጋጌዎች ይመራል።
#ጊዜያዊ ጉዳት: ጉዳቱ ጊዜያዊ ከሆነ፣ ስራ እስከሚጀምር ድረስ ሊያገኝ ይችል የነበረውን ያክል ካሳ ያገኛል።
#ከፊል ቋሚ ጉዳት: መስራት ባላስቻለው መጠን ልክ ይሰላል።
#ቋሚ ጉዳት: እስከ ጡረታ ጊዜው ድረስ ተሰልቶ ይሰጠዋል።
የአካል ጉዳት ሲደርስ፣ የወደፊት ጉዳት ካሳ ስሌት ላይ የደረሰውን የጉዳት መጠን፣ የሰራተኛውን የገቢ መጠን እና ተጎጂው ጡረታ ለመውጣት የቀረውን ጊዜ በደንብ ማጤን ያስፈልጋል።
2. የራሱን ስራ ለሚሰራ ሰው የሚሰጥ ካሳ
የራሱን ስራ እየሰራ ለሚተዳደር ሰው ካሳውን ለማስላት ገቢውን ለማወቅ አስቸጋሪ ሊሆን ቢችልም፣ የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም ወርሃዊ ወይም አመታዊ አማካይ ገቢውን በመመልከት ያጣውን ወይም ሊያጣ የሚችለውን ጥቅም በማስላት ካሳውን መተመን ይቻላል።
3. ስራ አጥ ለነበረ ሰው የሚሰጥ ካሳ
በህመም፣ ለመስራት ባለመፈለግ፣ የሚመጥነውን ስራ በማጣት ወይም በጠቅላላው ስራ አጥ በመሆን ስራ እየሰሩ ያልነበሩ ሰዎች ላይ ጉዳት ቢደርስባቸው የገቢውን መጠን ማወቅ ስለሚያስቸግር ካሳውን ማስላት ይከብዳል። በዚህ ጊዜ ዳኞች በፍትሃዊነት (በርትዕ) ካሳውን ለማስላት ይገደዳሉ።
4. በሞት ምክንያት የሚሰጥ ካሳ
በአደጋ ምክንያት ሞት ሲያጋጥም፣ ካሳ የመጠየቅ መብት ያለው ማነው የሚለው ወሳኝ ነው። የፍትሐ ብሔር ህግ ቁጥር 2095 መሰረት የሟች ባል/ሚስት፣ ወላጆች እና ተወላጆች ካሳ መጠየቅ ይችላሉ። ለእነዚህ ሰዎች የሚከፈለው ካሳ ቀለብ ስለሆነ፣ በቤተሰብ ህጉ መሰረት ቀለብ ጠያቂ ሊያሟላቸው የሚገቡ መስፈርቶችን ማሟላትና ማስረዳት ይጠበቅባቸዋል።
5. ለህሊና ጉዳት የሚሰጥ ካሳ
የህሊና ጉዳት የሰው ልጅ የውስጥ ስሜት ጉዳት በመሆኑ ካሳውን በገንዘብ መለካት አስቸጋሪ ነው። ሆኖም የህሊና ጉዳት ሲያጋጥም የገንዘብ ካሳ እንደሚከፈል በፍትሐ ብሔር ህግ ቁጥር 2105(1) ተቀምጧል።
የህሊና ጉዳት ካሳ የሚከፈለው በልዩ ሁኔታ በህግ ለተመለከቱ ጉዳቶች ብቻ እንጂ ሁልጊዜም ካሳ እንደማያስከፍል የፍትሐ ብሔር ህግ ቁጥር 2105(2) ይደነግጋል። የህሊና ጉዳት ካሳ የሚወሰነው ርትዕን መሰረት አድርጎ ሲሆን፣ የፍትሐ ብሔር ህግ ቁጥር 2106-2115 ይህንን ያብራራል። የህሊና ጉዳት ካሳ 1,000 ብር መብለጥ እንደሌለበት የፍትሐ ብሔር ህግ ቁጥር 2116(3) ያስቀምጣል።
የካሳ አከፋፈል ስርዓት
ጉዳት መድረሱ፣ ለጉዳቱ ማን ኃላፊነት እንደሚወስድና የካሳ ክፍያው መጠን ከተለየ በኋላ መወሰን ያለበት ሌላ ወሳኝ ጉዳይ የካሳ አከፋፈል ስርዓቱ ነው። የህግ ባለሙያው እንዳሉት፣ ሁለት አይነት የካሳ አከፋፈል ስርዓቶች አሉ፦
1. የቁርጥ ክፍያ
ይህ የካሳ ክፍያ የተወሰነበትን መጠን በአንድ ጊዜ ለባለመብቱ በመክፈል የሚፈጸም ነው። ይህ ዘዴ በብዙ ሀገራት የሚተገበርና መርህም ነው።
2. በየጊዜው የሚደረግ ክፍያ
መርሁ የጉዳት ካሳን በቁርጥ መክፈል ቢሆንም፣ በልዩ ሁኔታ ግን በየጊዜው እንዲከፈል ተደርጎ መወሰን እንደሚቻል በህጉ ተቀምጧል። ካሳን በየጊዜው እንዲከፈል ለመወሰን፣ የካሳው ባህሪ፣ የአካባቢ ሁኔታዎች እና የካሳ ከፋዩ ማረጋገጫ መስጠት ያለባቸው ነጥቦች ናቸው።
#Mikias_Melak
በማናቸውም ፍርድ ቤት ጠበቃ እና የሕግ አማካሪ
Alternative legal enlightenment & Service
https://linktr.ee/alehig
WhatsApp👉 #+251920666595
Telegram👉 @MikiasMelak
#የሕግ_መረጃ https://t.me/AleHig
#የሕግ_እውቀት alehig.com
#AleHig #አለሕግ #አለሕግ #ህግ
13