አለሕግAleHig ️
16.2K subscribers
2.84K photos
25 videos
1.86K files
3.56K links
ከጠበቃና የሕግ አማካሪ
አማራጭ የሕግ እውቀትና አገልግሎት
Alternative legal enlightenment & Service
Website: alehig.com
https://linktr.ee/alehig
WhatsApp👉 #+251920666595
Telegram👉 @MikiasMelak
የሕግ ምክርና ድጋፍ፣ የተለያዩ ህጎች፤ አዋጅ፣ ደንብ፣ መመሪያ፣ #የሕግ_መረጃ
Download Telegram
#ማሳሰቢያ_ቤት_ለሚገዙ_ለሚሸጡ

በአሁን ግዜ ቤት የሚገዙ፣ የሚሸጡ ሁሉ ስራቸው ህገወጥ ስለሆነ ከዚህ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ የሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ አገልግሎት አሳስቧል።
.
የቋሚ ንብረት ሽያጭ የቆመ ቢሆንም በአዲስ አበባ ከተማ አገልግሎቱ ሳይጀመር ሽያጭ እና ማስተላልፈ በመንደር ውል እና በውክል እየተሰራ መሆኑ ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 ዘግቧል።

የሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙሉቀን አማረ ፤ በውክልናም ሆነ በመንደር ውል የቤት ሽያጭ ማከናወን ህጉ እንደማይፈቅድ ገልፀዋል።
.
አገልግሎቱ የሚጀምርበትን ጊዜ እናሳውቃለን ብለዋል።

" ቤት ሽያጭ ውል ሰነድ የማረጋገጥ አገልግሎት ነው " ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ " ይህ ላልተወሰነ ጊዜ ተቋርጧል። ተቋሙ በተለይ ከአ/አ ከተማ አስተዳደር ጋር በመሆን ህገወጥ ይዞታዎችን የማረጋገጥ ስራ እየሰረ ስለሆነ ከዛ ጋር ተያይዞ ላልተገባ ሰዎች ያልተገባ ውል ውስጥ እንዳይገቡ ያን የማረጋገጥ ስራ እስኪጠናቀቅ በጊዜያዊነት አገልግሎቱን መስጥ ቆሟል " ሲሉ አስረድተዋል።

ይሄ ህገወጥ ይዞታዎችን የማጣራት ስራ እየተሰራ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ሙሉቀን ስራው እስኪጠናቀቅ ድረስ ላልተወሰ ጊዜ የማይንቀሳቀስ ንብረት ወይም መኖሪያ ቤት ሽያጭ / በስጦታ የማስተላለፍ ውሉ አሁንም ለጊዜው እንደተቋረጠ ይቀጥላል ሲሉ አሳውቀዋል።

ተቋሙ የተቋረጠውን አገልግሎት በሚጀምርበት ሰዓት በግልፅ በተለያየ ሚዲያ መረጃውን የሚሰጥ መሆኑን አመልክተዋል።

በተለይ የተጠራቀመ አገልግሎት ካለ ተገልጋዮች በሰልፍ ብዙ ሳንይገላቱ ለመስራት አሰራር ተዘርግቶ ይኬዳል ሲሉ ጠቁመዋል።

ህብረተሰቡ ላልተገባ የመንደር ውል ሆነ ባልተገባ መረጀ ላይ ተመስርቶ ከሚደረጉ ውሎች እንዲቆጠብ የሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ አገልግሎት ለሸገር ራድዮ በሰጠው ቃል አሳስቧል።
በይርጋ የማይታገዱ የፍትሀብሄር ጉዳዬች
=======//////========

የይርጋ መሰረታዊ ዓላማ ማንኛውም በህግ በግልፅ የተደነገገ መብትና ግዴታ በህጉ በተወሰነው ወይም በተገደበው ጊዜ ውስጥ ስልጣን ላለው አካል እንዲቀርቡ ግዴታን በማስቀመጥ መብቴ ተጣሰብኝ የሚል ወገን ዳተኛ ሳይሆን በትጋት መብቱን እንዲጠይቅ ለማስቻል መሆኑ ይታወቃል።

ነገር ግን አንዳንድ ጉዳዬች ከንብረቶቹ ልዩ ባህሪና የመንግስት ፖሊሲ አንፃር ህግ አውጪው በይርጋ እንዳይታገዱ አድርጎ ያስቀመጣቸው የፍትሀብሄር ጉዳዬች አሉ። ከእነዚህ መካከል፦

#የመፋለም ክስ ( petitory action)
~~××××××~~~~~

ለባለሀብቱ የባለቤትነት መብት ከሚሰጣቸው መብቶች መካከል ንብረቱ ያለ እርሱ ፈቃድ ከህግ ውጪ በሌላ ሰው ወይም ሀይል ከተወሰደ ንብረቱን ካለበት ድረስ በመከታተል የማስመለስ ወይም የመፋለም መብት አንዱ ስለመሆኑ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1206 ድንጋጌ ያስረዳል፡፡

ባለሀብትነትን የሚያስቀር የይርጋ ዘመን” በሚል ርዕስ ስር በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1192 የተመለከተው በሚንቀሳቀስ ንብረት ላይ ያለውን መብት በአስር ዓመት የጊዜ ወሰን /ይርጋ/ ቀሪ የሚሆንበትን አግባብ ያመላከተ ሲሆን የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለሀብትነት በይርጋ ቀሪ እንደሚሆን ግን አያሳይም፡፡

ድንጋጌው የሚንቀሳቀስ ንብረትን የባለሀብትነት ጥያቄ የጊዜ ገደብ ካስቀመጠ በኋላ ስለማይንቀሳቀስ ንብረት ባለሀብትነት ቀሪ መሆን በዝምታ ያለፈው ለጉዳዩ ቀጥተኛ ተፈፃሚነት በሌለው በፍ/ብ/ህግ አንቀፅ 1845 ስር የተመለከተው ተመሳሳይ የ10 ዓመት የይርጋ ጊዜ ተፈፃሚ እንደሆን ተፈልጎ ካለመሆኑ በላይ የማይንቀሳቀስ ንብረት ከሚንቀሳቀስ ንብረት በተለየ ሁኔታ የዘላቂነት ባህሪ ያለው እና ከትውልው ወደ ትውልድ የሚተላለፍ በመሆኑ የባለሀብትነቱ መብት ቀሪ የሚሆነው በይርጋ ሳይሆን በሌሎች ሁኔታዎች( አንቀፅ 1168....) ይሆን ዘንድ ተፈልጎ የተቀመጠ ድንጋጌ መሆኑን እንገነዘባለን።

በመሆኑም የማይንቀሳቀስ ንብረት የመፋለም ክስ (petitory action) በይርጋ ቀሪ አይሆንም። (የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰ/መዝ/ቁ 43600)

N.B= ይህ ሲባል ግን ከውርስ፣ ከሽያጭ፣ ከስጦታና ከሌሎች ውሎች በመነጨ በማይንቀሳቀስ ንብረት ላይ የሚደረግ ክርክር ይርጋ የለውም ማለት የሚቻል ሳይሆን ለጉዳዩ አግባብነት ባላቸው ህጎች በተቀመጡ የይርጋ ጊዜዎች የሚስተናገዱ ይሆናል።

#ህገ ወጥ ውል (unlawful contrat)
~~~×××××~~~~~~

እንድ ውል የፀና ውል ለመሆን መሟላት ከሚገባው አንዱ ነጥብ ውሉ ህጋዊ በሆነ ጉዳይ ላይ የተመሰረተ መሆን የሚገባው እንደሆነ የፍ/ብ/ህግ 1678 ይደነግጋል። አንድ ውል ህገ ወጥ ውል ነው የሚባለው ደግሞ ተዋዋዬቹ የተዋዋሉበት መሰረታዊ ጉዳይ ዓላማ በመሰረታዊና ሞራላዊ ይዘቱ ተዋዋይ ወገኖች ስምምነት በማድረግ መብትና ግዴታ እንዲፈጥሩበት በህግ ያልተፈቀደ ወይም በህግ ክልከላ የተደረገበት ሆኖ ሲገኝ ነው።

አንድ ውል የተመሰረተበት መሰረታዊ ጉዳይ (object of contract) በህግ ክልከላ የተደረረበት በሆነ ጊዜ ውሉ በህግ ፊት እንደሌለና ምንም አይነት ህጋዊ ውጤት የማያስከትል (null and void contrat) እንዲሁም ችግሩን በማስተካከል ህጋዊ ውጤት እንዲኖረው ማድረግ የማይቻል ነው። ለምሳሌ፦ የመሬት ሽያጭ ውል፣ በሰው ለመነገድ የተደረግ ውል፣ ወንጀል ለመፈፀም የተደረገ ውል......
ህገ ወጥ የሆነውን ውል ውድቅ ለማድረግ ደግሞ በህጉ የተደነገገው የይርጋ ጊዜ ገደብ መቃወሚያ ሊቀርብ የማይችልና ተቀባይነት የሌለው በመሆኑ በይርጋ የሚታገዱ አይደሉም። (የፌ/ጠ/ፍ/ቤት/ሰ/መዝ/ቁ 43226)

N.B= ይህ ሲባል ግን የህጉን መስፈርት ያላሟሉ ውሎች (illegal contract) ከህገ ወጥ ውል በተለየ ሁኔታ ታይተው የይርጋ ድንጋጌዎች ተፈፃሚ የሚሆንባቸው መሆኑን መረዳት ይገባል።

#የመንግስትን መሬት የማስመለስ ክስ
~××××××~~~~~~

ግለሰቦች በፌደራሉ እና በክልሉ መንግስት በወጡ የገጠር መሬት አጠቃቀም እና አስተዳደር አዋጅ በሚደነግጉት መሰረት በህጋዊ መንገድ ሳይሰጣቸው ከህግ ውጪ የወል ወይም የመንግስትን መሬት ይዘው መቆየታቸው እና የመሬቱ ባለይዞታ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር ማግኘታቸው የመሬቱ ህጋዊ ባለይዞታ ሊያደርጋቸው አይችልም። በወረራ የተያዘ የመንግስት መሬትም ይርጋ የሌለው መሆኑን የአብክመ የገጠር መሬት አዋጅ ቁጥር 252/2009 አንቀፅ 55 በግልፅ ያስቀምጣል።

በመሆኑም ከህግ ውጭ በህገ ወጥ መንገድ የተያዙ መሬቶችን መኖራቸውን ሲረዳ መሬት አስተዳደርም ሆነ የመንግስት ወኪል የሆነ አካል መሬቶቹን ለማስመለስ የሚያቀርበው ክስ በይርጋ የሚታገድ አይደለም። (የፌ/ጠ/ፍ/ቤት/ሰ/መዝ/ቁ 93013 እና 96203 ያልታተሙ)

#በህገ ወጥ መንገድ የተያዘ የግለሰብ ይዞ መሬት
~~××××××~~~~~~

ከላይ እንደተመለከትነው ህገ ወጥ ውልን መሰረት አድርጎ የግለሰብን መሬት በያዘ ሰው ላይ የሚቀርብ ክስ ይርጋ የሌለው መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በአብክመ የገጠር መሬት አዋጅ ቁጥር 252/2009 አንቀፅ 55 መሰረት ህጉ በማይፈቅድበት መንገድ በሀይልም ሆነ በህገ ወጥ አግባብ የገጠር መሬትን ይዞ የተገኘ ግለሰብ ላይ የሚቀርብ ክስ ይርጋ የለውም።

N.B= በህገ ወጥ መንገድ የሚለው ሀሳብ በህግ ተቀባይነት በሌለው አኳኋን የያዘን በሚመለከት እንጂ የህጉን መስፈርት ባላሟላ ውል ወይም ተግባር (illegal contrat) አማካኝነት የተያዘን መሬት የሚመለከት አይደለም። ምክንያቱም መሬቱን የያዘው በህጉ በተፈቀደ የውል ተግባር ሆኖ የሚፈለገውን ፎርማሊቲ ወይም መስፈርት አለማለቱ ብቻ አያያዙ ህገ ወጥ ነው የሚያስብል ስላልሆነ ነው።

#የአደራ ውል
~×××

አደራ ተቀባይ በአደራ የሚጠብቀውን ዕቃ የሚመልስበት የጊዜ ገደብ በውል ተመልክቶ ከሆነ ይህ ጊዜ ሲያበቃ ዕቃውን መመለስ ያለበት ስለመሆኑ በፍ/ብ/ህ/ቁ 2781(1) የተመለከተ ሲሆን በውል ላይ የተቀመጠ የጊዜ ገደብ ከሌለ ግን አደራ ሰጪው እንደጠየቀ ወዲያውኑ እንደሚመለስ በፍ/ብ/ህ/ቁ 2989(1) ስር ተመላክቷል።

ከእነዚህ ድንጋጌዎች ለመረዳት የሚቻለው አደራ ተቀባይ ዕቃውን የሚመልስበት የጊዜ ገደብ ከሌለ በቀር አደራ ሰጪው በአደራ እንዲቀመጥ የሰጠው ዕቃ ያለምንም የጊዜ ገደብ በማንኛውም ጊዜ እንዲመለስለት መጠየቅ የሚችል መሆኑን ነው።

#የውርስ ሀብት ክፍፍል
~~~~××××~~~~

ወራሾች ተለይተው እና የውርስ ሀብቱ ድርሻ ታውቆ ነገር ግን ክፍፍል ሳይደረግ የቆየን የውርስ ሀብት በማናቸውም ጊዜ መጠየቅ እንደሚችልና በይርጋ የሚታገድ እንዳልሆነ ከፍ/ብ/ህ/ቁ 1060 እና ተከታዬቹ ድንጋጌዎች መረዳት ይቻላል።

እንዲሁም ከውርስ ሀብት ጥያቄ ጋር በተያያዘ የውርስ ሀብቱን በእጁ አድርጎ በመገልገል ላይ ያለ ተከራካሪ የሆነ ወራሽ ለክርክሩ ምክንያት የሆነውን የውርስ ንብረት በጋራ ይዞ ከቆየ ሰው ላይ የውርስ ድርሻዬን ልወቅ ወይም ይለይልኝ ጥያቄ በይርጋ ይታገዳል የሚባልበት አግባብ የለም።

#የድምፅ ብክለት
~×××~~
የድምፅ ብክለት ክልከላ ባለቤቱ ስራውን የሚፈፅመው በራሱ ንብረት ወይም ቤት ውስጥ ቢሆንም ድርጊቱ ሌላውን ጎረቤት እንዳይረብሽ፣ እንዳያውክ፣ ወይም ችግር እንዳያስከትል በማድረግ መብቱን ይጠቀም ዘንድ ህጉ ያበጀው የባለቤትነት መብት አጠቃቀምን አድማስ የሚወስን ስርዓት መሆኑን ከአንቀፅ 1226 እና ተከታዬቹ ድንጋጌዎች መረዳት ይቻላል።

ይህን ችግር ለማስወገድ የሚቀርበው አቤቱታ ከፍ/ብ/ህ/ቁ 1149 ስር ከተመለከተው በይዞታ ላይ ሁከት መፍጠር ተግባር የሚለይ ሲሆን አንዴ የተፈጠረ የድምፅ ብክለት እንዲቀጥል የሚደረግበት አግባብ ስለሌለ በይርጋ የሚታገድ አይደለም።
ከሄኖክ ታዬ በማንኛውም ፍ/ቤት ጠበቃና የሕግ አማካሪ ገፅ ተወሰደ
🟢 @lawsocieties
🟡 @lawsocieties
🔴 @lawsocieties
https://t.me/lawsocieties
ሕገ-ወጥ ደረሰኝ መጠቀም የሚያስከትለው ቅጣት
💥💥💥💥💥💥💥💥
ደረሰኝ በዕቃ ወይም በአገልግሎት ግብይት ላይ ተመሥርቶ ከሻጩ/ አቅራቢው ለገዥው የሚሰጥና ግብይት ስለመፈፀሙ፣ ገንዘብ ስለመሰብሰቡ፣ ዋጋው ስለመከፈሉ ወይም ለወደፊት ለመክፈል ውል መግባቱን የሚያሳይ ሰነድ ነው፡፡
ደረሰኝ የሚሰጠው ጠቀሜታ ሰፋ ያለ ቢሆንም በዋነኛነት በተለያዩ አካላት መካከል የሚፈፀመውን ግብይት ግልጽና በማስረጃ ላይ የተመሠረተ ለማድረግ የሚሰጠው ጠቀሜታ በጣም የጐላ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ የንግድ ሥራ እንቅስቃሴውን ውጤት የሚያሳየው የሂሳብ መዝገብ ተቀባይነት ባላቸው የሂሳብ አያያዝ መርሆዎች ላይ ተመሥርቶ ቢዘጋጅም እንኳ ለምዝገባው መሠረት የሚሆኑት ደረሰኞች አጥጋቢ ካልሆኑ በሂሳብ ውጤቱ ተጠቃሚ በሆነው አካል ላይ ሊያስከትል የሚችለው ኪሳራ ቀላል አይደለም፡፡
ይህን ኪሳራ ለመቀነስ እና የህግ ተገዢነትን ለማሳደግ የታክስ አስተዳደር ስርዓቱ የራሱ የሆነ ህግ እና ደንብ አለው በዚህም መሰረት ማንኛውም ሰው የተጭበረበሩ ደረሰኞችን ያዘጋጀ፣ ያተመ፣ የሸጠ ወይም ያሰራጨ ወይም የታክስ ዕዳውን ለመቀነስ ወይም ተመላሽ ለመጠየቅ የተጭበረበሩ ደረሰኞችን የተጠቀመ እንደሆነ ብር 100ሺ እና ከ7-10 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እሥራት ይቀጣል፤
ሀሰተኛ ደረሰኞችን፣ ለማዘጋጀት/ለማተም የሚያገለግል ማሽን፣ መሳሪያ፣ ወይም ሶፍትዌር የያዘ፣ የሸጠ፣ ያከራየ ወይም በሌላ መንገድ ያቀረበ ማንኛውም ሰው ብር 200ሺ የገንዘብ ቅጣት እና ከ10-15 ዓመት ጽኑ እሥራት ይቀጣል፤
ሀሰተኛ ደረሰኞችን የያዘ፣ ያስቀመጠ፣ ለሽያጭ ያመቻቸ ወይም ሀሰተኛ ደረሰኞች ጥቅም ላይ እንዲውሉ ያደረገ ሰው ከ3-5 ዓመት በሚደረስ ጽኑ እሥራት ይቀጣል፤
ግብይት ሳይፈጸም ደረሰኝ የሰጠ ወይም የተቀበለ ሰው ከብር 100ሺ እስከ ብር 200ሺ ቅጣት እና ከ7-10 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እሥራት ይቀጣል፤
#ለበለጠ መረጃ የፌደራል የታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 983/2008 ይመልከቱ።
🟢 @lawsocieties
🟡 @lawsocieties
🔴 @lawsocieties
ሀሰተኛ ሰነድ ማዘጋጀት፣ መገልገል እና የወንጀል ተጠያቂነት
1. ሀሰተኛ ሰነድ እና አይነቱ
ሀሰተኛ ሰነድ ማዘጋጀትና መገልገል የሀገርን ኢኮኖሚ እንዲሁም የዜጎችን መብትና ጥቅም ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርስ የወንጀል ተግባር ነው፡፡ ሀሰተኛ ሰነዶች ዝግጅት በረቀቀና እውነተኛውን በሚመስል መንገድ የሚፈፀም በመሆኑ ይህን ከባድ ወንጀል ለመከላከልና አጥፊዎችን ለመቅጣት ብሎም ህብረተሰቡ ከዚህ ወንጀል እራሱን እንዲጠብቅ ግንዛቤ መፍጠር ያስፈልጋል፡፡

ሀሰተኛ ሰነድ ማዘጋጀቱ በመንግስታዊና ህዝባዊ ድርጅቶች ሰነዶች ላይ የሚፈፀም ከሆነ በሙስና ወንጀል የሚያስጠይቅ ነው፡፡ መንግስታዊ ሰነድ ሲባል የሚኒስቴር መስሪያ ቤት ወይም የክልል ቢሮዎችና በየደረጃው ያሉ አስተዳደር መስሪያ ቤቶች የወጡ በማስመሰል የሚዘጋጅ ሲሆን ለምሳሌ የንግድ ወይም ኢንቨስትመንት ፈቃድ ወረቀቶች፣ የይለፍ ወረቀቶች፣ የብቃት ማረጋገጫዎች፣ የስራ ፈቃድ ወረቀቶች፣ የስራ ልምድ፣ የክፍያ ማዘዣዎች፣ የባለቤትነት ማረጋገጫ ካርታ ወይም ሊብሬዎች፣ ወዘተ የሚያካትት ነው፡፡ የህዝባዊ ድርጅቶች ሰነድ ደግሞ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ወይም ተቋማት ሰነዶች ለምሳሌ የመጋዘን ደረሰኝ፣ የእቃ ማውጫ ፈቃድ፣ የትምህርት ማስረጃ፣ የባንክ ክፍያ ሰነዶች እና መሰል በእነዚህ ተቋማት የሚሰጡ ሰነዶችን የሚመለከት ነው፡፡ እነዚህን ሰነዶች ማዘጋጀትና መገልገል የሚያስከትለውን የወንጀል ተጠያቂነት ከዚህ እንደሚከተለው በዝርዝር ይቀርባል፡፡

2. ሀሰተኛ ሰነድ ማዘጋጀት፣ መገልገል እና የሚያስከትለው የወንጀል ተጠያቂነት
ማንኛውም ሰው የሌላውን ሰው መብት ወይም ጥቅም ለመጉዳት ወይም ለራሱ ወይም ለሌላ ሰው ተገቢ ያልሆነ ማናቸውም መብት ወይም ጥቅም ለማስገኘት በማሰብ አንድ ፅሁፍ፣ መዝገብ ወይም ማንኛውም ሰነድ የመንግስት ወይም የህዝባዊ ድርጅት በማስመሰል ያዘጋጀ ወይም የፈጠረ፤ በመንግስት ወይም በህዝባዊ ድርጅት መዝገብ፣ ፅሁፍ ወይም ሰነድ የሰፈረን እውነተኛውን ፅሁፍ በመለወጥ ወይም በመደለዝ፣ በሀሰተኛ ፊርማ፣ በእጅ በተደረገ ምልክት ወይም በጣት ፊርማ፣ በማህተም ወይም የሌለውን ስልጣን ወይም ችሎታ እንዳለው አስመስሎ በመፈረም ሀሰተኛ ሰነድ የፈጠረ እንደሆነ፤ አንድን የመንግስት ወይም የህዝባዊ ድርጅት ሰነድ በተለይ የፈራሚውን ስም ወይም ፊርማ ወይም የሰነዱን ይዘት፣ አሃዝ፣ ፍሬ ነገር ወይም ዝርዝር መግለጫ በሙሉ ወይም በከፊል በመለወጥ፣ በማሻሻል፣ በመቀነስ ወይም በመጨመር ወይም በማጥፋት ወደ ሀሰተኛነት የለወጠ ወይም ማናቸውንም ሀሰተኛ ፍሬ ነገር ያስገባ ወይም እንዲገባ ያደረገ እንደሆነ በሙስና ወንጀሎች አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀፅ 23 መሰረት ከሶስት አመት እስከ አስር አመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ያስቀጣል፡፡
በተጨማሪም የዚህ ወንጀል አፈፃፀም በሚከተለው ሁኔታ ሊከብድ የሚችል ሲሆን ይኽውም ሰነዶቹን እንዲያዘጋጅ፣ እንዲመዘግብ እንዲጠብቅ ወይም ከነዚሁ ውስጥ ቅጂዎችን እንዲሰጥ ሀላፊነት በተሰጠው የመንግስት ወይም የህዝባዊ ድርጅት ሰራተኛ እንደሆነ ወይም ሰነዱን በመገልገል የተገኘው ጥቅም ከፍተኛነት ወይም በግለሰብ፣ በመንግስት ወይም በህዝባ ድርጅት ወይም በህዝብ ጥቅም ላይ ያደረሰው ጉዳት ከፍተኛ እንደሆነ ቅጣቱ ከአምስት አመት እስከ ሀያ አምስት አመት የሚደርስ እስራት ያስቀጣል፡፡

ሌላው መገንዘብ የሚገባን ጉዳይ የሙስና ወንጀሎች አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀፅ 23 (4) መሰረት በወንጀል የሚያስጠይቀው ሀሰተኛ ሰነዶችን ማዘጋጀት ብቻ ሳይሆን ይዞ መገኘትና መገልገል ጭምር ሲሆን በዚህም መሰረት ወደ ሀሰት የተለወጠ ወይም በሀሰት የተዘጋጀ ሰነድ በቤቱ፣ በተሽከርካሪው፣ በኪሱ ወይም በማንኛውም አግባብ በቁጥጥሩ ስር የተገኘ እንደሆነ ከላይ በተጠቀሰው ቅጣት ጋር ተመሳሳይ በሆነ ይቀጣል፡፡ በተጨማሪም ማንኛውም ሰው ወደ ሀሰት በተለወጠ ወይም በሀሰት በተዘጋጀ ሰነድ እያወቀ የተገለገለበት እንደሆነ በተመሳሳይ ይቀጣል፡፡

በሉላ በኩል ከግብር አከፋፈል ጋር በተያያዘ ማንኛውም ሰው ሆን ብሎ ወይም በከባድ ቸልተኝነት ለገቢዎች ሚኒስቴር የተጭበረበሩ ሰነዶችን ያቀረበ በፌዴራል ታክስ አስተዳደር አዋጅ 983/2008 አንቀፅ 118 መሰረት ከሶስት እስከ አስራ አምስት አመት በሚደርስ እስራት ይቀጣል፡፡ በአንቀፅ 119 መሰረት ደግሞ እነዚህን የተጭበረበሩ ደረሰኞችን ያዘጋጀ፣ ያተመ፣ የሸጠ ወይም ያሰራጨ ወይም የተጠቀመ ከሰባት አመት እስከ አስር አመት በሚደርስ እስራት ይቀጣል፡፡ የዚህን ወንጀል አፈፃፀም ለመከላከል ሲባል የተደነገገ ሌላ ጥፋት ሀሰተኛ ደረሰኞችን ለመስራት፣ ለማዘጋጀት ወይም ለማተም የሚያገለግል ማሽን፣ መሳሪያ ወይም ሶፍትዌር የያዘ፣ የሸጠ፣ ያከራየ ወይም በሌላ መንገድ ያቀረበ ማንኛውም ሰው ከአስር እስከ አስራ አምስት አመት እስራት እንደሚቀጣ በህጉ መደንገጉ ነው፡፡ በተመሳሳይ እነዚህን ሀሰተኛ ደረሰኞችን የያዘ፣ ያስቀመጠ፣ ለሽያጭ ያመቻቸ ወይ ሀሰተኛ ደረሰኞችን ጥቅም ላይ እንዲውሉ ያደረገ ከሶስት እስከ አምስት አመት እስራት ይቀጣል፡፡

ከጉምሩክ መንግስታዊ ስራዎች ጋር በተያያዘ ማንኛውም ሰው በጉምሩክ ኮሚሽን ላይ ጉዳት ለማድረስ ወይም ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ ኮሚሽኑ የሚጠቀምበትን ቅፅ፣ ማህተም፣ መታወቂያ፣ አርማ፣ የጉምሩክ ማሸጊያ ወይም ማናቸውም ሰነድ ወይም ምልክት ወደ ሀሰተኛነት የለወጠ ወይም አስመስሎ የሰራ ወይም ይህንኑ ያከፋፈለ፣ የተጠቀመ ወይም ለመጠቀም የሞከረ ወይም ለጉምሩክ ስነ ስርአት የሚቀርቡ ሰነዶችን የሰረዘ፣ የደለዘ፣ የፋቀ ወይም አስመስሎ የሰራ በጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 859/2006 አንቀፅ 167 እና በጉምሩክ አዋጅ ማሻሻያ አዋጅ 1160/2011 አንቀፅ 169(4) መሰረት ከአምስት እስከ አስር አመት እስራት ይቀጣል፡፡

ከላይ ከተመለከቱት መንግስታዊና ህዝባዊ ሰነዶችን ማዘጋጀትና መገልገል ወንጀል በተጨማሪ በእለት ተእለት የኑሮ እንቅስቃሴ የምንጠቀምባቸውን ግላዊ ሰነዶችን በሀሰተኛ መንገድ ማዘጋጀትና መገልገል ከለይ ከተመለከተው ከባደ ሁኔታ ዝቅ ባለ በመለስተኛ ደረጃ በወንጀል የሚያስጠይቅ ነው፡፡ በዚህም መሰረት ጥቅም ወይም መሻሻልን ለማግኘት ወይም ለማስገኘት በማሰብ ተገቢ መብት ለማስገኘት የሚችሉ ፅሁፎችን፣ ግላዊ ሁኔታን የሚገልፁ ማስረጃዎችን ወይም ምስክርነትን ማስረጃዎችን ወይም ማናቸውንም አይነት ጉዳይ የሚመለከቱ የምስክርነት ማረጋገጫ ሰነዶችን ወደ ሀሰተኛነት የለወጠ ወይም አስመስሎ የሰራ ወይም እያወቀ ይህን የመሰለውን ሰነድ እንዲገለገልበት ለሌላ ሰው መስጠት በ1996 ዓ/ም የወንጀል ህግ አንቀፅ 385 መሰረት በቀላል እስራት ወይም መቀጮ ያስቀጣል፡፡ ይህ ሰነድ የግል ጉዳይን የያዘ እንደሆነ ከአንድ አመት ባልበለጠ እስራት፣ ወይም ሰነዱ ህዝባዊ ባህሪ ያለው ሆኖ እንደመታወቂያ ወረቀት ወይም የልደት ምስክር ወረቀት ወይም የችግርተኛነት፣ የመልካም ጠባይ፣ የብቁነት ወይም ብቁ አለመሆን ማረጋገጫ ምስክርነት ወይም የህዝብ መዝገብ ወይም መቆጣጠሪያ ቅጂ እንደሆነ ከሶስት ወር በማያንስ እስራት ያስቀጣል፡፡

በሌለ በኩል ወንጀሉን የፈፀመው እነዚህን ሰነዶች እንዲያዘጋጅ፣ እንዲያስቀምጥ፣ እንዲጠብቅ ወይም እንዲሰጥ ሀላፊነት በተሰጠው የመንግስት ሰራተኛ እንደሆነ እና ይህን ወንጀል ያደረገው በሌላ ሰው መብት ላይ ጉዳት ለማድረስ ሳያስብ እንደሆነ ከስድስት ወር እስከ አምስት አመት በሚደርስ እስራት ወይም በመቀጮ ወይም በሁለቱም ያስቀጣል፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ማንኛውም ሀኪም፣ የጥርስ ሀኪም፣ የመድሀኒት ቅመማ ባለሙያ፣ የእንስሳት ሀኪም፣ አዋላጅ ወይም በህክምና ሙያው ህክምናን በሚመለከት የምስክር ወረቀት ለመስጠት መብት ያለው ማንኛውም ሌላ ሰው የምስክር ወረቀት ስራ ላይ እንደሚውል እያወቀ ለተቀባዩ ሰው የማይገባ ጥቅም ለማስገኘት የሚችል ወይም የሌላውን ሰው ህጋዊ ጥቅም የሚጎዳ ሀሰተኛ የህክምና ምስክር ወረቀት አዘጋጅቶ ፅፎ የሰጠ በወንጀል ህግ አንቀፅ 387 መሰረት በቀላል እስራት ወይም በመቀጮ ይቀጣል፡፡ ይህ ወንጀል በመንግስት ሰራተኛ ከተፈፀመ ወይም ወንጀሉ በስጦታ ወይም በሌላ ጥቅም የተፈፀመ ከሆነ ቅጣቱ ከአስር እስከ አስራ አምስት አመት እስራት ይደርሳል፡፡ በመጨረሻም ማንም ሰው ህገ ወጥ በሆነ መንገድ ሊገለገልባቸው በማሰብ ኦፊሴላዊ ፅሁፎችን፣ የምስክር ወረቀቶችን፣ ዲፕሎማዎችን ወይም ሰነዶችን ወደ ሀሰተኛነት ለመለወጥ ወይም በሀሰት ለመፍጠር የሚያገለግሉ መሳሪያዎችንና መስሪያዎችን ወይም ቁሳዊ ነገሮችን የሰራ፣ በእጁ ያስገባ፣ የያዘ፣ የሰጠ ወይም ለሽያጭ ወይም ለስጦታ ያቀረበ እንደሆነ በአንቀፅ 390 መሰረት ከአምስት አመት በማይበልጥ እስራት እና በመቀጮ ይቀጣል፡፡

በአጠቃላይ ከላይ ከተመለከቱት የሀሰተኛ ሰነድ ማዘጋጀትና መገልገል ወንጀሎች ሰፊ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገባና ህብረተሰቡ ከእነዚህ ወንጀሎች እራሱን ማራቅና መጠበቅ ያስፈልጋል፡፡ እነዚህ ወንጀሎች በሀገርና በህብረተሰቡ ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርሱ ሲሆን የዜጎችን መብትና ጥቅም በማጭበርበር የሚያሳጡ ናቸው፡፡ በህግም የሚያስከትሉት ተጠያቂነት ሰፊና ከባድ ነው፡፡ ስለሆነም ሀሰተኛ ሰነዶች ከማዘጋጀት፣ እንዲዘጋጅ ከማድረግ፣ ይዘን ከመገኘት፣ ከመገልገል፣ ሀሰተኛ ሰነድ መስሪያ መሳሪያዎችን ይዞ ከመገኘት መቆጠብ ያስፈልጋል፡፡ በተጨማሪም እንዲህ ያለ ጥፋት መፈፀሙን ስናስተውል ለህግ አስከባሪ አካላት ማሳወቅ እና ተጠያቂነት እንዲኖር ለማድረግ መተባበር ያስፈልጋል፡፡
🟢 @lawsocieties
🟡 @lawsocieties
🔴 @lawsocieties
https://t.me/lawsocieties