አለሕግAleHig ️
16.2K subscribers
2.83K photos
25 videos
1.86K files
3.55K links
ከጠበቃና የሕግ አማካሪ
አማራጭ የሕግ እውቀትና አገልግሎት
Alternative legal enlightenment & Service
Website: alehig.com
https://linktr.ee/alehig
WhatsApp👉 #+251920666595
Telegram👉 @MikiasMelak
የሕግ ምክርና ድጋፍ፣ የተለያዩ ህጎች፤ አዋጅ፣ ደንብ፣ መመሪያ፣ #የሕግ_መረጃ
Download Telegram
በሰብአዊ መብቶች ጥበቃ የዐቃቤ ሕግ ሚና‼️‼️🔴
=========================
ዐቃቤ ሕግ በሕግ ጠባቂነቱ መንግስት የሚያወጣቸውን የተወሰኑ ሕጐች መከበራቸውን የሚያረጋግጥ የመንግስት አካል ነው፡፡ ሕግን የተላለፉ ሰዎችን ለሕግ በማቅረብ ሕግና ስርዓት በሕብረተሰቡ ውስጥ እንዲሰፍን ማድረግ ዋነኛ የዐቃቤ ሕግ ተግባር ነው፡፡ ይህ የመንግስት አካል እንደሌሎች የመንግስት ተቋማት ሁሉ የእለት ተዕለት ስራውን ሲያከናውን በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ መንግስት የተረጋገጡ የዜጐች ሰብአዊ መብቶችና መሠረታዊ ነፃነቶች የማክበርና የማስከበር ኃላፊነት አለበት፡፡

በመሆኑም በመንግስት ተቋምነቱ ከሌሎች የመንግስት አካላት ጋር ያለው ህገ መንግስቱን የማክበርና የማስከበር የወል ኃላፊነት እንደተጠበቀ ሆኖ ዐቃቤ ሕግ በሕግ አስከባሪነቱ እና ጠባቂነቱ ለሕግ የበላይነት እና ለሰብአዊ መብቶች ጥበቃ በወንጀል ፍትህ አስተዳደር ውስጥ ከፍተኛ ሚና መጫወት ይኖርበታል፡፡

የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ እኤአ ሴፕቴምበር 1990 ባወጣው የዐቃብያነ ሕግ ሚናን በሚመለከት መመሪያ(UN Guidelines on the Role of prosecutors) በወንጀል ፍትህ ሂደት ያላቸውን ከፍተኛ ሓላፊነት በተመለከተ በአንቀጽ 12 ስር አቃብያነ ህግ በህጉ መሰረት ግዴታቸውን ፍትሃዊ በሆነ ሁኔታ መወጣት እንዳለባቸው ከማስቀመጡ በተጨማሪ ሰብዓዊ ክብርን የመጠበቅ፣ ሰብአዊ መብቶችን የማክበርና እንከን የሌለው የወንጀል የፍትህ ስርአት እንዲኖር አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚኖርባቸው አስቀምጧል፡፡

ከተጠቀሰው የተባበሩት መንግስታት መመሪያ በሚቀራረብ ሁኔታ ዐቃቤ ሕግ ሰብአዊ መብቶች እንዲከበሩ በፍትህ ስርዓቱ ውስጥ የሚያደርገው አስተዋፅጾ ከምርመራ አንስቶ የተጠርጣሪው ጥፋተኝነት ተረጋግጦ ቅጣት እስኪጣልበት ወይም ንፁህ መሆኑ እስኪረጋገጥ ድረስ ሊዘልቅ እንደሚችል በብሄራዊ ህጎችም ተደንግጎ ይገኛል፡፡ ይህንንም እንደሚከተለው በዝርዝር እናያለን፡፡

1. #ዐቃብያነ ሕግ ከፖሊስ ምርመራ ጋር በተያያዘ ስላለባቸው ኃላፊነት

በሕብረተሰብ ውስጥ ሰላምን የሚያደፈርስ እንቅስቃሴ ወይም ሕገወጥ ተግባር ተፈጽሞ ሲገኝ አጥፊዎችን ለፍርድ ለማቅረብ የወንጀል ምርመራ ስራ በዋነኛነት በፖሊስ አካላት እንደሚካሄድ የታወቀ ነው፡፡ የወንጀል ምርመራ ስራ ሂደት በባህሪው የዜጐችን መብት የመገደብ ወይም የመንካት ሁኔታ የሚያስከትል በመሆኑ ከዜጐች የሰብአዊ መብቶች ጥበቃ አንፃር በጥንቃቄ ሊከናወን የሚገባው ተግባር ነው፡፡

የወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 8/2/ ዐቃቤ ሕግ ተግባሩን በሚያከናውንበት ጊዜ አስፈላጊ የሆነውን ትዕዛዝና መመሪያ ለፖሊስ የመስጠትና ፖሊስ በሕጉ መሠረት ግዴታውን መወጣቱን ማረጋገጥ እንዳለበት መደንገጉ ፖሊስ የምርመራ ስራውን ሲያከናውን የግለሰቦችን ሰብአዊ መብቶች ባከበረና በሕግ በተወሰኑ ስርዓቶች መሰረት ኃላፊነቱን መወጣቱን ዐቃቤ ሕግ እንዲቆጣጠር የታለመ እንደሆነ ይታመናል፡፡

በቅርብ አመታት ወጥተው በፌዴራል መንግስት ተፈፃሚ ከሆኑ ሕጐች መካከልም የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አዋጅ ቁጥር 313/95 እና የኢፌዲሪ አስፈፃሚ አካላትን ስልጣንና ተግባር ለመወሰን የወጣው አዋጅ ቁጥር 471/98 ዐቃቤ ሕግ የፖሊስን ተግባር ሕጋዊነት የሚቆጣጠርበት ድንጋጌ አካተዋል፡፡ በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አዋጅ ቁጥር 313/95 አንቀፅ 7/9/ ፌዴራል ፖሊስ “የወንጀል ምርመራን በተመለከተ ከፌዴራል ዐቃቤ ሕግ የሚሰጠውን ትዕዛዝ” እንደሚፈፅም የተደነገገ ሲሆን በአዋጅ ቁጥር 471/98 አንቀፅ 23/3/ ስር ደግሞ ፍትህ ሚኒስቴር (ፌዴራል ዐቃቤ ሕግ)

“በፌዴራል ፍርድ ቤቶች ስልጣን ስር የሚወድቁ ወንጀል ተፈፅሟል ብሎ ሲያምን ምርመራ እንዲደረግ ያዛል፣ በቂ ምክንያት ሲኖር የተጀመረ ምርመራ እንዲቆም ወይም ተጨማሪ ምርመራ
እንዲከናወን ያደርጋል...”

በማለት ደንግጓል፡፡ በዚህ ድንጋጌ መሰረት የፌዴራል ዐቃቤ ሕግ ከተለያዩ አካላት ወንጀል ስለመፈፀሙ ጥቆማ ሲደርሰው፣ ፖሊስ አላግባብ ምርመራ አላጣራም አለኝ የሚል አቤቱታ ሲቀርብለት ወዘተ ምርመራ እንዲጀመር ለፖሊስ ትዕዛዝ የሚሰጥ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ከሕግ ውጪ ምርመራ እየተጣራብኝ ነው የሚል አቤቱታ ሲቀርብለት እና በሌሎች ምክንያቶች አላግባብ በፖሊስ የተጀመሩ ምርመራዎች መኖራቸውን ካረጋገጠ የተጀመረ ምርመራ እንዲቋረጥ ትዕዛዝ ሊሰጥ ይችላል፡፡ የክልል ዐቃቤ ሕግ ተቋማትም የክልል ፖሊሶች ከሚፈፅሙት የምርመራ ተግባር ጋር በተያያዘ ተመሳሳይ ስልጣን እንዳላቸው ይታመናል፡፡

ከላይ ከቀረቡት ዝርዝር ድንጋጌዎች ዐቃቤ ህግ በራሱ ህግ አስፈጻሚ ብቻ ሳይሆን የፖሊስ አባላትም የዜጐችን ሰብአዊ መብቶች የሚመለከቱ ሕግጋት በትክክል ማክበራቸውን የማረጋገጥ ኃላፊነት እንዳለበት እና በሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ቁልፍ የሆነ ድርሻ እንዳለው ለመረዳት ይቻላል፡፡

2. #ዐቃብያነ ህግ ከክስ ጋር በተያያዘ ስላለባቸው ኃላፊነት ዐቃቤ ሕግ በፖሊስ ተጣርቶ የቀረበለትን የምርመራ መዝገብ በማየት
የዜጐችን የተፋጠነ ፍትህ የማግኘት መብት ግምት ውስጥ ባስገባ ሁኔታ፡-

ተጨማሪ ደጋፊ ማስረጃ ሊገኝ ይችላል ብሎ ካመነ ተጨማሪ ምርመራ እንዲደረግ በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 38/ሐ/ መሠረት ለፖሊስ ትዕዛዝ የማስተላለፍ፣
ተጠርጣሪን ጥፋተኛ ለማድረግ የሚያስችል በቂ ማስረጃ የለም ብሎ ካመነ ደግሞ በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 42/1/ሀ/ መሠረት ክስ ያለማቅረብ ወይም
ክስ ለመመስረት እና ተከሳሽን ለማስቀጣት የሚያስችል በቂ ማስረጃ አለ ብሎ ካመነ ደግሞ ክስ በማዘጋጀት ስልጣን ላለው ፍርድ ቤት በማቅረብ ተገቢውን ክርክር የማድረግ ግዴታ አለበት፡፡

ዐቃቤ ሕግ በተከሳሽ ላይ ክስ የሚያቀርበው ሕዝብን በመወከል ስለሆነ፣ የሕዝብ ጥቅም የሚጠበቀው ጥፋተኞች ሲቀጡ እና ንፁህ የሆኑ ሰዎች ከክስ ነፃ ሲሆኑ በመሆኑ በመጀመርያ ክስ ለመመስረት በቂ ማስረጃ መኖሩን የማረጋገጥ፣ በክሱ መሰማት ሂደት የተከሳሽን ንፁህ መሆን የሚያረጋግጡ ማስረጃዎች ካገኘ ወይም ጥፋተኛ ሊያስደርጉ የሚችሉ ማስረጃዎች በሂደት የጠፉ ከሆነ ወዘተ ደግሞ ክሱን ማንሳት ይጠበቅበታል፡፡ፀጋዬ ደመቀ ሎየር ገፅ ተገኘ
#join #join #Share #Share #Share
https://t.me/lawsocieties
🟩 @lawsocieties
🟨 @lawsocieties
🟥 @lawsocieties