አለሕግAleHig ️
16.2K subscribers
2.85K photos
25 videos
1.86K files
3.56K links
ከጠበቃና የሕግ አማካሪ
አማራጭ የሕግ እውቀትና አገልግሎት
Alternative legal enlightenment & Service
Website: alehig.com
https://linktr.ee/alehig
WhatsApp👉 #+251920666595
Telegram👉 @MikiasMelak
የሕግ ምክርና ድጋፍ፣ የተለያዩ ህጎች፤ አዋጅ፣ ደንብ፣ መመሪያ፣ #የሕግ_መረጃ
Download Telegram
በወንጀል ክርክር ወቅት የመስቀለኛ ጥያቄ መጠየቂያ መርሆችና ቴክኒኮች
========================
ዐቃቤህግ በመደበኛ የወንጀል ክስ ለመስቀለኛ ጥያቄ ሂደት ሲቀርብ ስለጉዳዩ በተለይም ስለምስክርነቱ አስቀድሞ ሳይዘጋጅ ማለትም ዕዉቀት ሳይኖረዉ ነዉ:: መስቀለኛ ጥያቄ ሂደት እንኳንስ ያለቅድመዝግጅት ዝግጅትም ተደርጎ አስቸጋሪ ሥራ ነዉ::
የመከላከያ ምስክሮች ከመዋሸት እስከ ሆን ብሎ አለማስታወስ ድረስ መሰናክል ሊፈጥሩ ይችላሉ:: በመስቀለኛ ጥያቄ ሂደቱ ለዐቃቤህግ ተባባሪ ላይሆኑ ይችላሉ::
ስለዚህ ዐቃቤህግ በዚህ ሂደት ለማግኘት የሚፈልገዉን ምናልባትም ሊያገኝ የሚገባዉን ያለማግኘት ችግር ሊያጋጥመዉ ይችላል:: እንዲያዉም የራሱን ክስ ሊጎዳ የሚችል አጋጣሚ ሊፈጠር ይችላል::
ስለዚህ መስቀለኛ ጥያቄን ለማካሄድ ወይም ላለማካሄድ በከፍተኛ ጥንቃቄ መምረጥ አና ማካሄድ የግድ ነዉ:: ለዚህ ደግሞ አንዳንድ መርሆችንና ቴክኒኮችን ማወቅ ተገቢ ነዉ:: እነዚህ መርሆችና ቴክኒኮች በአሰራር ልማድ የምንፈጥራቸዉን ችግሮች ለማረም እገዛ ሊያደርጉ የሚችሉ ናቸዉ:: እነዚህን ቆየት ብለን የምናያቸዉ ሆኖ ከዚያ በፊት ስለመስቀለኛ ጥያቄ ሂደት ወሰን እና መጠን አንዳንድ ነገሮች እንይ::
በቅድሚያ ከላይ እንደተገለጸዉ መስቀለኛ ጥያቄ አስቸጋሪ ሂደት ነዉ:: አደጋዎቸ አሉት:: ስለዚህ መስቀለኛ ጥያቄ ማከሄድ ተመራጭ ላይሆን ይችላል:: መስቀለኛ ጥያቄ አለማካሄድ ምን ዉጤት አለዉ? በወ/መ/ህ/ሥ/ሥ/ቁ. 140 እንደተመለከተዉ መስቀለኛ ጥያቄ አለመጠየቅ በሌላዉ ወገን የተነገረዉን እንደማመን አያስቆጥርም:: ስለዚህ መስቀለኛ ጥያቄ ብዙም ባይደፈር ይመረጣል:: በተለይም የመስቀለኛ ጥያቄ ግብ ከሆኑት (የተቃራኒን ምስክርነት የማይታመን መሆኑን ማሳየት በክሱ ላይ የደረሰዉን ጉዳት ማስተካከል ወዘተ) አንዱን ወይም ከዚያ በላይ ለማሳካት የምንችል ወይም ተገቢ ካልሆነ በቀር ወይም ምስክሩ ለጉዳያችን የምንፈልገዉ መረጃ ብቸኛ ምንጭ ካልሆነ በቀር መስቀለኛ ጥያቄ ማካሄድ የሚመከር አይደለም::
ሆኖም ዘወትር እንደሚስተዋለዉ አንዳንድ ምስክሮች ባህሪያቸዉ ምንም ሳይጠየቁ መሄድ የለባቸዉም የሚያስብል ይሆናል:: በዚህ ጊዜ መስቀለኛ ጥያቄ ማንሳት የግድ ከሆነ ከላይ ሲባል እንደነበረዉ አደጋዉ የበዛ በመሆኑ መጠኑን ማሳነስ ይመከራል::
በወ/መ/ህ/ሥ/ሥ/ቁ. 137(3) ስር መስቀለኛ ጥያቄ በዋና ጥያቄ ጊዜ በተመለሱ ነገሮች ዉስጥ ያለዉን ስህተት አጠራጣሪ ወይም የማይታመን ቃል ለፍርድ ቤቱ ለመግለጽ ወይም ለማስተባበል የሚደረግ መሆኑ ተደንግጓል:: ስለዚህ ከዚህ የወጣ ጥያቄ ሲነሳ ተቃዉሞ ሊገጥም ይችላል:: ሆኖም በዋና ጥያቄ ከተፈጠረዉ ድንበር ወጥቶ መጠየቅ የሚቻልባቸዉ የተለዩ አጋጣሚዎች ይኖራሉ:: ለምሳሌ የምስክሩን ተዓማኒነት የሚመለከቱ ጥያቄዎች በዋና ጥያቄ ጊዜ ባይነሱም በጠቅላላዉ ምስክሩ የተናገረዉን ነገር ተዓማኒነት የሚመለከት ስለሚሆን ተቀባይነት ያለዉ አካሄድ ነዉ:: ለምሳሌ የተለመደዉ የተከሳሽ መከላከያ ክርክር (በወንጀሉ ጊዜ በወንጀሉ ቦታ አልነበርኩም) ሲቀርብ የሚነገረዉ ታሪክ የተፈጸመበትን ጊዜ ከወንጀሉ ጊዜ ጋር እንዲገጥም የማድረግ ነገር ስለሚኖር ምስክሩ ጊዜን በመለየት ረገድ ስላለዉ ችሎታ ለማረጋገጥ በዚህ ዙሪያ ጥያቄ ቢነሳ ሊከለከል አይገባም:: ምስክሩ ተዓማኒነቱ ምን ያህል እንደሆነ ለማሳየት የሚረዳ በመሆኑ ተገቢ ነዉ::

ከተዓማኒነት ጋር በተያያዘ ምስክሩ በነገሩ ዉስጥ ያለዉ ጥቅም ወይም ፍላጎት ሊታለፍ የማይገባዉ ነጥብ ነዉ:: ምስክሩ የሚሰጠዉ ምስክርነት ከነገሩ ዉስጥ ካለዉ ጥቅም ወይም ፍላጎት የተነሳ ከዕዉነት የራቀ ሊሆን ይችላል:: ስለዚህ በነገሩ ዉስጥ ጥቅም እንዳለዉ ማሳየት በሰጠዉ ምስክርነት ላይ ዕምነት እንዲታጣ ሊያደርግ ስለሚችል በዋና ጥያቄ አልተነሳም ተብሎ ቀሪ ሊደረግ አይገባም::
አንዳንዴ ምስክሩ ራሱ ለመስቀለኛ ጥያቄ በሚመልስበት ጊዜ በዋና ጥያቄ ጊዜ ላልተነሱ ሀሳቦች መንገድ ሊከፍት ይችላል:: በዚህ ጊዜ ምስክሩ ራሱ ባነሳዉ ነገር ላይ ሌላ መስቀለኛ ጥያቄ የማይጠየቅበት ምክንያት አይኖርም:: ስለዚህ ዐቃቤህግ እነዚህን አጋጣሚዎች በንቃት መጠባበቅ ይገባዋል፣ ለዚህም ምስክርነቱን በሚገባ ማዳመጥ ይኖርበታል፡፡
ከጭብጥ ከመዉጣት ሌላ በመስቀለኛ ጥያቄ ሂደት የማይፈቀድ ነገር ምስክርን ማስፈራራት እና ማንጓጠጥ ነዉ:: ምስክሩ ዐቃቤህግ የሚፈልገዉን እንዲል መገደድ የለበትም:: ይህን ማድረግ የሚቻለዉ ክህሎት በተሞላዉ የአጠያየቅ ዘዴ መሆን አለበት:: አዘዉትሮ በፍርድቤቶች በሚደረግ ክርክር ጊዜ የሚስተዋል በህግ ባለሙያዎች (ዐቃብያነህግ ጠበቆች ዳኞች) የሚባል አንድ ነገር አለ:: ምስክሩ እነዚህ ባለሙያዎች እንደፈለጉት ወይም ዕዉነት ነዉ ብለዉ እንደሚያስቡት ሳይናገር በቀረ ጊዜ በሃሰት መመስከር በወንጀል እንደሚያስቀጣ ይነግሩታል:: ይህ ነገር ማስፈራራት ከመሆኑ በተረፈ ነገሩ ተሰምቶ ሳያልቅ እና ምስክሩ የተናገረዉ ሃሰት ይሁን ዕዉነት ሳይረጋገጥ በጉዳዩም ላይ በምስክሩም ላይ ፍርድ የመስጠት ያህል ይሆናል:: ከዐቃቤህግ የህግ ጠባቂነት ሚና አኳያም የሰዉን መብት የሚደነግጉ ህጎችን የመጣስ ዉጤት ይኖረዋል::

የመስቀለኛ ጥያቄዎች ባህሪያት (መሪ ጥያቄ)፡-- ይህ የጥያቄ አይነት በመስቀለኛ ጥያቄ ሂደት ዉስጥ በህግ የተፈቀደ ቢሆንም ዐቃቤህግ (ሌሎች ባለሙያዎችም) ሲጠቀሙበት አይስተዋልም:: በርግጥ ይህ የጥያቄ አይነት ስለሚያስከትለዉ መልስ ማወቅን ስለሚጠይቅና ዐቃቤህግ ደግሞ ከላይ እንደተገለጸዉ ያለቅድመዝግጅት ስለሚቀርብ ይህን የጥያቄ አይነት ለመጠቀም አይደፋፈርም:: ሆኖም ዋና ጥያቄ የሚመስል ሂደት በማካሄድ ነገሮችን እንዲደገሙ ከማድረግና በዚህም ችሎትን ከማሰላቸት ግፋ ሲልም የዐቃቤህግን ክስ የሚያፈርስ አጋጣሚ ከመፍጠር በዚያዉ በችሎት በተደረገች ዝግጅትም ቢሆን መሪ ጥያቄ በመጠየቅ ምስክሩን እንዳሻዉ እንዳይናገር መቆጣጠር ይመከራል:: በመስቀለኛ ጥያቄ ሂደት ዋናዉ ግብ ምስክሩን መቆጣጠር የሚመሰክረዉን ነገር መወሰን በዚህም ለመዋሸት ያለዉን ዝንባሌ ወዘተ ማስቀረት ነዉ:: በዋና ጥያቄ ጊዜ ሊነሱ የሚገባቸዉ ዝግ ያልሆኑ ጥያቄዎችን በማንሳት ምስክሩ የሚናገረዉን ነገር ልቅ ማድረግ ሂደቱን ዐቃቤህጉ ሳይሆን ምስክሩ እንዲቆጣጠረዉ ማድረግ ይሆናል::

አጭርና ነጠላ ጥያቄ፡- የተከሳሽን ምስክር በመስቀለኛ ጥያቄ መቆጣጠር የሚቻልበት መንገድ ጥያቄዉን መሪ ጥያቄ በማድረግ ብቻ አይደለም:: ጥያቄዉን አጭር ማድረግም እንዲሁ በምስክሩ ላይ የበላይነትን ያስገኛል:: ጥያቄዉ ከአንድ በላይ ሃሳብ ከሌለዉ እና ርዝመቱም አጭር ከሆነ ምስክሩ ለዚሁ ብቻ መልስ እንዲሰጥ ሰለሚገደድ ብዙም መፈናፈኛ አይኖረዉም:: በተለይ ከአንድ በላይ ሃሳብ አለመያዙ ምስክሩ መርጦ የመመለስ ስራ እንዳይሰራ ያደርገዋል የመልሱ ወሰን የታጠረ ይሆናል::
ከዚህ በተያያዘ ከአንድ በላይ የሆኑ ጥያቄዎችን አነባብሮ በአንድ ጊዜ መጠየቅ የሚገኘዉን መልስ ግልጽ እንዳይሆን ያደርገዋል:: አንድ መልስ ቢሰጥ ለየትኛዉ ጥያቄ እንደተመለሰ ማወቅ አይቻልም:: ስለዚህ እንደዋና ጥያቄ ጊዜ በአንድ ጊዜ አንድ ጥያቄ ብቻ ማንሳት ተገቢ ይሆናል::
መልሱ የሚታወቅ (የሚረጋገጥ) ጥያቄ፡- የመስቀለኛ ጥያቄ መልሱ የሚታወቅ ወይም ማስረጃ ሊቀርብበት የሚችል መሆን ይኖርበታል:: ግን ቀደም ሲል እንደተገለጸዉ ትልቁ ችግር ስለመከላከያ ምስክርነትም ሆነ ስለምስክሩ አስቀድሞ የሚሰበሰብ ማስረጃ የለም:: ስለዚህ የዐቃቤህግ መስቀለኛ ጥያቄዎች በዕድል ባወጣ ያዉጣዉ ወዘተ ላይ ተመስርተዉ የሚጠየቁ ናቸዉ:: ሆኖም ማስረጃ በተሰበሰበባቸዉ አጋጣሚዎች ለምስክሩ የሚቀርብ መስቀለኛ ጥያቄ ሊመለስ የሚገባዉን መልስ የሚጠቁም ሊሆን ይገባል:: ለዚህ ጥያቄ የሚሰጠዉ መልስ ምንም ይሁን ምን በቂ ስለሚሆን የሚገኘዉ መልስ ምንነት ስጋት አይፈጥርም:: የሚፈለገዉን መልስ ምስክሩ አመነም አላመነም ዉጤቱን አይቀይረዉም:: ምክንያቱም ቢያምን ዐቃቤህግ እንደሚፈልገዉ ሆነለት ማለት ሲሆን ከካደ ደግሞ ማስረጃ ስላለ ምስክርነቱን ማስተባበልና በዚህም ምስክሩ ተዓማኒነት የሌለዉ መሆኑን ማሳየት ይቻላል::

የመስቀለኛ ጥያቄዎች አደረጃጀት፡- ዉጤታማ መስቀለኛ ጥያቄ በጥያቄዎች አይነት ብቻ የሚወሰን አይደለም:: የጥያቄዎቹ ቅደም ተከተልም (ቅንብር) የራሱ አስተወጽዖ ይኖረዋል:: በተለይ በመስቀለኛ ጥያቄ ጊዜ ምስክሩን በሚገባ መቆጣጠር እጅግ አስፈላጊ ከመሆኑ አኳያ የጥያቄዎቻችን አወቃቀር ይህን የመቆጣጠር ችሎታ የሚያሳጣ መሆን የለበትም:: ስለዚህ የተቃራኒ ወገንን ምስክር የምንጠይቅ እንደመሆኑ በቀላሉ የምንፈልገዉን ነገር ለማግኘት አስቸጋሪ ስለሚሆን የጥያቄዎቻችን አወቃቀር የምስክሩን ወዳጅነት የሚያስገኝ እንዲሆን የግድ ነዉ::
ዐቃቤህግ መስቀለኛ ጥያቄ ሊጠይቅ ከወሰነ በዚህ ጥያቄ ሊያሳካ የፈለገዉን ነገር በሂደቱ መጀመሪያ ላይ መግለጽ የለበትም:: ይህ ግብ በምስክሩ ከታወቀ የተቃራኒ ወገን ምስክር እንደመሆኑ የመስቀለኛ ጥያቄዉ ሂደት ወደዚህ ግብ እንዲደርስ መፍቀዱ አጠራጣሪ ነዉ:: ስለዚህ ይህን ግብ የሚደብቅ የጥያቄዎች ቅደምተከተል መኖር አለበት::
ከዚህ የተነሳ በመነሻዉ ላይ የሚጠየቁ ጥያቄዎች ከምስክሩ ጋር ፍጥጫን የማያስነሱ ምስክሩ በቀላሉ ሊያምናቸዉ ወይም ሊስማማባቸዉ የሚችሉ ፍሬነገሮችን የሚመለከቱ መሆን ይገባቸዋል:: ይህን ማድረግ በዐቃቤህጉና በተከሳሽ ምስክር መካከል ሰላማዊ ሁኔታ ይፈጥራል:: ስለዚህ ከምስክሩ የሚፈለገዉን ለማግኘት ቀላል ይሆናል ቢያንስ ምስክሩ መሰናክሎችን ከመፍጠር ይታቀባል::
ይህ ማለት ደግሞ ዐቃቤህግ ለክሱ እጅግ አስፈላጊ የሚላቸዉን ነጥቦች መጀመሪያ ላይ ማንሳት የለበትም ማለት ነዉ:: እነዚህን ጉዳዮች ከመነሻዉ ከገለጸ ምስክሩ የመስቀለኛ ጥያቄዉን ዓላማ በቀላሉ ማወቅ ስለሚችል እና ይህም ምስክሩ በዋና ጥያቄ ጊዜ ከተናገረዉ ሊቃረን ስለሚችል ምስክሩ ይህን የተፈለገ ነገር ለመስጠት አይፈቅድም:: በሚችለዉ መንገድ ራሱን ከመቃረን ለማዳን የማስተካከያ መረጃዎችን ከመግለጽ ያለፈ ነገር ለመፈጸም ፈቃደኛ እንዳይሆን ያደርገዋል:: ስለዚህ ዐቃቤህግ መነሻዉ ላይ ከዋና ጥያቄ ሂደት በተቃራኒ ዋና ነጥቦችን ሳይሆን ዝርዝር ጉዳዮችን (በተቻለ መጠን ምስክሩ የማይክዳቸዉን) እንዲያነሳ ይመከራል::
ከዚህ ሌላ ዐቃቤህግ የመስቀለኛ ጥያቄ ዓላማዉን ለመደበቅ በጥያቄና መልሱ ሂደት ጊዜ ከአንድ የጥያቄ ሃሳብ ወደሌላዉ በመዝለል ምስክሩ የነገሩን አቅጣጫ እንዳይገነዘብ ማድረግ ይችላል:: ለዚህም ጥያቄዎቹ በተለያየ ርዕስ ስር እንዲደራጁ ሊያደርግ ይገባል:: ከዚህ ጋር በተያያዘ የአካባቢ ማስረጃን አስመልክቶ ከዋና ጥያቄ ጋር በማያያዝ ያነሳነዉ ሃሳብ ለመስቀለኛ ጥያቄም አግባብነት ይኖረዋል:: በመስቀለኛ ጥያቄ ጊዜ ዓላማዉ ምስክሩ የዐቃቤህግን የክርክር አቅጣጫ እንዳይገነዘብ ማደረግ በመሆኑ የአካባቢ ማስረጃን የሚመለከቱ ጥያቄዎች እነዚህን ማስረጃዎቸ በአንድ ላይ የማሰባሰብ ባህሪ እንዳይኖራቸዉ ማድረግ ያስፈልጋል:: ምክንያቱም ከተሰባሰቡ ትርጉማቸዉ ግልጽ ስለሚሆን ምስክሩ የክርክሩን አቅጣጫ በቀላሉ እንዲረዳዉ በማድረግ መሰናክል እንዲፈጥር ይገፋፋዋል:: ስለዚህ መስቀለኛ ጥያቄዎች የአካባቢ ማስረጃዎች እንዲበታተኑ የማድረግ ችሎታ ሊኖራቸዉ ይገባል:: ለዚህም ከላይ እንደተመከለተዉ የጥያቄዎችን ቅድም ተከተለ በማዘባረቅ ከርዕስ ወደርዕስ መዟዟር አስፈለጊ ነዉ::
ከጥያቄዎች ቅደም ተከተል ጋር በተያያዘ አዘዉትሮ የሚታይ ስህተት አለ:: በመስቀለኛ ጥያቄ ጊዜ ምስክሩ ሊክዳቸዉ የማይችሉ ፍሬነገሮችን መሰረት በማድረግ ዐቃቤህግ ለሚያቀርባቸዉ ጥያቄዎች በሚገኙ መልሶች የሚገነባ ታሪክ ሊኖር ይችላል:: ከዚህ በኋላ የዚህን ሁሉ ጥያቄና መልስ እንድምታ (ድምዳሜ) ምስክሩ እንዲናገር ከተጠየቀ መልሱ የተከሳሹን ክርክር የሚጎዳ ከመሰለዉ ወይም ከሆነ ምስክሩ የጥያቄዉ አቅጣጫ ሰለሚገባዉ ቀደም ሲል የሰጣቸዉን መልሶች የሚያስተካክል መልስ ሊሰጥ ስለዚህ ለክሱ የሚረዳዉን ነገር የመደበቅ ተግባር ሊፈጽም ይችላል:: ይህም እንኳ ባይሆን ተከሳሹ ወይም ጠበቃዉ በክርክሩ ላይ በመስቀለኛ ጥያቄ ጊዜ የደረሰዉን ጉዳት በድጋሚ ጥያቄ ጊዜ የማስተካከል ስራ እንዲሰራ የማባነን ዉጤት ይኖረዋል:: ይህም ካልሆነ ፍርድቤቱ ራሱ በማጣሪያ ጥያቄ ጊዜ ነገሩን እንዲያነሳ ምስክሩም በዚህ አጋጣሚ ነገሩን የሚያድበሰብስ ወይም የሚያርም ተግባር እንዲፈጽም የማስታወስ ዉጤት ይኖረዋል:: በተግባር ሲደረግ የሚስተዋለዉም እንዲህ ያለ ዉጤትን የሚያመጣ አጠያየቅ ነዉ::
ስለዚህ ይህን የነገሩን ማሰሪያ ጥያቄ ዐቃቤህግ መጠየቅ የለበትም:: ቀላልና ተራ በሚመስሉ ጥያቄዎች የተገነባዉ ታሪክ እንድምታ ለፍርድቤቱ የሚተዉ ነዉ:: ምናልባት ለፍርድቤቱ ግልጽ የማይሆን ቢሆን በመስቀለኛ ጥያቄ የተሰጡ መልሶች የሚጠቁሙት ድምዳሜ ምን እንደሆነ በክርክር ማቆሚያ ንግግር ጊዜ መግለጽ ይቻላል::
ነገር ግን አሁን ባለዉ አሰራር ይህ ከላይ የተመለከተዉ የአሰራር አቅጣጫ ምን ያህል ያስኬዳል? የሚል ጥያቄ ማንሳት ተገቢ ነዉ:: ምክንያቱም የክርክር መዝጊያ ንግግር ወይም በተለምዶ አጠራሩ የመፋረጃ ሃሳብ እንዲቀርብ የሚያደፋፍሩ ፍርድቤቶች ጥቂት ከመሆናቸዉም በላይ እንዲቀርብ የሚያደርጉትም ቢሆኑ በአብዛኛዉ በጽሁፍ እንዲቀርብ የሚያደርጉ ሰለሆነ እንዲሁም የቀረበዉን ሃሳብ የሚጠቀሙበት ማለትም በዉሳኔ ጊዜ ከግምት የሚያስገቡት ፍርድቤቶች በእጀጉ ጥቂት በመሆናቸዉ ዐቃቤህግ በመስቀለኛ ጥያቄ ጊዜ ያስመሰከራቸዉ ፍሬነገሮች ድምር ዉጤት ምን እንደሆነ በክርክሩ ጊዜ (በመስቀለኛ ጥያቄ ማጠናቀቂያ ጊዜ) ካልጠቆመ እንዲህ የሚያደርግበት መድረክ አያገኝም:: ከዚህ የተነሳ ዐቃቤህግ ከተከሳሽ ምስክር ጋር በመስቀለኛ ጥያቄ ሂደት ዉስጥ ወይም ማሳረጊያ ላይ የምስክርነቱን እንድምታ እመን አትመን እሰጥ አገባ ዉስጥ ሲገባ ይታያል:: ስለዚህ ፍርድቤቶች የክርክር ማቆሚያ ንግግርን አሰራር እንዲያከብሩ ዐቃቤህግ መወትወት ዳኞችም ይህን አሰራር ባህል እንዲያደርጉት የግድ ነዉ::
ከዚህ በላይ ያየናቸዉ የጥያቄ አደረጃጀት ስራዎች ብቸኛ አይደሉም:: በርከት ያሉ በተለያዩ በለሙያዎች የሚቀርቡ ዘዴዎች አሉ:: ሆኖም ከላይ ያነሳናቸዉ ዘዴዎች ከኛ የአሰራር ልምድ ጋር ቁርኝት ስላላቸዉ ሊጠቀሱ በቅተዋል::
ሌሎች ቴክኒኮች፡- በመስቀለኛ ጥያቄ ጊዜ ቅድመዝግጅት ካለ ጥያቄዎችን በጽሁፍ አዘጋጅቶ የመቅረብ ነገር ሊኖር ይችላል:: ነገር ግን እንዲህ አይነቱ አቀራረብ መልካም አይደለም:: ጥያቄዎቹ በጽሁፍ ከተዘጋጁ ወይ እያነበቡ ለመጠየቅ ነዉ አለያም ሸምድዶ ከሃሳብ እያስታወሱ ለመጠየቅ ነዉ:: ሁለቱም ተመሳሳይ ናቸዉ:: ወረቀት ላይ የምናተኩር ከሆነ ወይም በአዕምሯችን ስለምናስታዉሰዉ ነገር የምናስብ ከሆነ ምስክሩን ዓይንለዓይን አንገናኝም ማለት ነዉ:: በመስቀለኛ ጥያቄ ጊዜ ከምስክሩ ጋር የዓይንላይን ግንኙነት መኖር ምስክሩን ለመቆጣጠር ይረዳል:: ከዚህም ሌላ ያልተጠበቁ ለክሱ የሚጠቅሙ አጋጣሚዎችን ለመጠቀም በጥያቄና መልሱ ሂደት ላይ ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል:: ጥያቄን ከወረቀት ላይ ወይም ከአዕምሮ ዉስጥ ማንበብ ይህን አትኩሮት ስለሚነፍግ በዚህም ረገድ ዐቃቤህግ ብሎም ክሱ ተጎጂ ይሆናሉ:: በተለይ ጥያቄዉ በርከት ያለ ከሆነ አንዱ ጥያቄ ተመልሶ ሌላ ለመጠየቅ በዝርዝሩ ዉስጥ የሚቀጥለዉ ጥያቄ ቦታ እንዳይጠፋ በማሰብ አትኩሮትን ወደዚሁ ጽሁፍ ለማድረግ መገደድ ይኖራል::
ከዚህ የተሻለዉ አማራጭ ጥያቄዉን በዝርዝር አለመጻፍ ነዉ:: ዝግጅቱ የግድ በጽሁፍ መሆን ካለበት የጥያቄዎቹን ሃሳቦች የያዙ ርዕሶችን ዝርዝር (አዉትላይን) አዘጋጅቶ መቅረብ ይመረጣል:: ርዕሶቹን ብቻ ከወረቀቱ ላይ በመመልከት ጥያቄዎቹን ከራስ ማመንጨት ይገባል::

አትኩሮትን ወደጥያቄና መልሱ ሂደት ማድረግ ተገቢ ስለመሆኑ ከፍ ብሎ ተጠቅሷል:: ከዚህ በተያያዘ ለመሰቀለኛ ጥያቄ የሚሰጡ መልሶችን ዐቃቤህግ ማድመጥ ይኖርበታል:: ለክሱ ገንቢ የሆኑ አጋጣሚዎችን ለመጠቀም የሚረዳ ከመሆኑም በላይ ምስክሩ ጥያቄዉን እየሸሸ የሚመልስ ከሆነ ይህን አስተዉሎ ጥያቄዉ እንዲመለስ ለማስገደድ (ምስክሩን ለመቆጣጠር) የሚያስችል ነዉ:: ከዚህ ከማድመጥ የሚያሰናክለዉ አንዱ ከላይ እንደተመለከትነዉ ጥያቄን በዝርዝር ጽፎ ቀርቦ በንባብ መጠየቅ ሲሆን ሌላኛዉ ደግሞ ምስክርነቱን በዝርዝር መጻፍ ነዉ:: ሰለዚህ እነዚህን የአሰራር ዘዴዎች ወይም ባህሪዎች ዐቃቤህግ ሊያስወግድ ይገባል::
አንዳንድ ጊዜ የተቃራኒ ወገን ምስክር ሳያስበዉ ወይም ከዐቃቤህግ የአጠያየቅ ብቃት የተነሳ ለክሱ ጠቃሚ ምስክርነት ሊስጥ ይችላል:: በሌሎች አጋጣሚዎች ደግሞ ክሱን የሚጎዳ ነገር ሊመሰክር ይችላል:: በዚህ ጊዜ ዐቃቤህግ እንደተሰጠዉ ምስክርነት ጠቃሚነት ወይም ጎጂነት ስሜቱ የሚለዋወጥ ከሆነ ምስክሩ በሰጠዉ ምስክርነት እያደረሰ ያለዉን ዉጤት በሚገባ እንዲገነዘብ ስለሚያደርገዉ የተከሳሹን ክርክር የሚጎዳዉን ምስክርነት ያስተካክላል የዐቃቤህግን ክስ የጎዳበትን ምስክርነት በማጠናከር የበላይነቱን ይዞ የክርክሩን ሂደት የመቆጣጠሩን ሚና ከዐቃቤህግ ይነጥቃል::
የተከሳሽ ምስክር ለዐቃቤህግ ክስ ገንቢ የሆነ ምስክርነት ከሚሰጥባቸዉ አጋጣሚዎች አንዱ መዋሸት ነዉ:: መዋሸቱን የምናዉቅ ከሆነ ከምስክርነቱ በተቃራኒ የሆነዉን ዕዉነተኛዉን ታሪክ የሚያሳይ ማስረጃ አለን ማለት ነዉ:: ስለዚህ ምስክሩ ሲዋሽ ካገኘነዉ በዚሁ ዉሸቱ እንዲቀጥልበት የሚያደርጉ ጥያቄዎችን ማንሳት እንጂ መዋሸቱን ያወቅንበት መሆኑን የሚገልጽ ምንም ነገር ማድረግ የለብንም:: ምክንያቱም ይህን ከገለጽን የዋሸበትን ሁኔታ ያስተካክላል ስለዚህ ዐቃቤህግ ምስክሩ የማይታመን ወይም የሚዋሽ መሆኑን የሚያስረዳበትን አጋጣሚ ያጣል ማለት ነዉ::
በብዙ አጋጣሚዎች አላዋቂ መስሎ ላለመታየት በሚደረግ ጥረት ክርክርን መጉዳት ሊከተል ይችላል:: ስለዚህ በማያዉቁት ጉዳይ ጥያቄ ከመጠየቅ አለመቦዘን ተገቢ ነዉ:: ለምሳሌ በባለሙያ ምስክርነት ጊዜ ለባለሙያዉ ወይም ስለጉዳዩ ዕዉቀት ላላቸዉ ሰዎች ተራ የሆነ ነገር ሁሉ ለዐቃቤህግ ግልጽ ላይሆን ይችላል:: ስለዚህ አላዋቂ ላለመምሰል የባለሙያ ምስክርነት በሚነገርበት ጊዜ ነገሩ እንደገባዉ ሰዉ ዝም ብሎ ማዳመጥ ጉዳቱን ማወቅ የሚቻለዉ ነገሩ ካለቀ በኋላ ሰለሚሆን ጥንቃቄ ይፈልጋል:: በዚህ ረገድ ግልጽ ያልሆነን ነገር ማብራሪያ እንዲሰጥበት መጠየቅ ሊያሳፍር አይገባም ምንም ያህል ተራ ነገር ቢሆን ወይም ቢመስል::
ቀደም ሲል ለማየት እንደተሞከረዉ መስቀለኛ ጥያቄ አደጋ ያለዉ ሂደት ነዉ እንደተገኘ የሚገባበት አይደለም:: ጥንቃቄ ያሻዋል:: ተመራጭ ሆኖ ወይም አማራጭ የሌለዉ ሆኖ ጥያቄዉ መካሄድ ያለበት ከሆነ የተመጠነ ሊሆን ይገባዋል:: በዚህ ጊዜ ምስክሩን ለመቆጣጠር መቻል ያስፈልጋል:: ለዚህም የማያጨቃጭቁ ጥያቄዎችን ማንሳት አንዱ ከምስክሩ ጋር ያለመፋጠጥ ሁኔታ መፍጠሪያ መንገድ ሲሆን ሌላዉ የጥያቄዉን ሂደት ዓላማ መደበቅ መቻል ነዉ:: ይህ ማለት ግን ምስክሩን ማፋጠጥ ወይም ማስጨነቅ በማንኛዉም አጋጣሚ ተገቢ አይደለም ማለት አይደለም:: ተቃራኒ ምስክር እንደመሆኑ የምንፈልገዉን ነገር በቀላሉ ሊሰጠን አይችልም ወይም አይፈቅድም:: ስለዚህ አንዳንድ ጊዜ ፍጥጫ አስፈላጊ ሊሆን ይችላል:: ትልቁ ጥያቄ ግን መቼ የሚለዉ ነዉ:: ይህን ነገር መቼ ማድረግና አለማድረግ እንዳለብን የምናዉቅባቸዉን አንዳንድ ሁኔታዎች መለየት ያስፍልጋል::
ምስክርን ማስጨነቅ ወይም ማፋጠጥ ተገቢ የሚሆንበት ጊዜ ምልክቶች - የምስክሩ መረጋጋት አለመቻል ከጠበቃዉ ርዳታን መጠበቅ መናደድ ወይም ማድበስበስ መጀመር የጠበቃዉ ማደናገሪያ ወይም አቅጣጫ ማስቀየሪያ ተቃዉሞዎች መበራከት - እነዚህና መሰል ሁኔታዎች ምስክሩ ለማፋጠጥ የተጋለጠ መሆኑን ጠቋሚ ናቸዉ:: በዚህ ጊዜ ምስክሩ የደበቀዉን ለማዉጣት ወይም ነገሮችን ማሳሳት ወይም ማዘባረቅ ጀምሮ ከሆነ የበለጠ ነገር የሚያበላሽበት ሁኔታ ዉስጥ መሆኑን መረዳትና ማፋጠጡን ማጠንከር ያስፈልጋል::
በዚህ ሁኔታ የተጀመረ ማፋጠጥ ቢኖርም ምስክሩ እየጠነከረ ከመጣና በቀላሉ የሚፈታ ሰዉ ካልሆነ ማፈግፈግ - መተዉ ተመራጭ ነዉ::
ምስክሩን ማፋጠጥ ተገቢ የማይሆንባቸዉ አጋጣሚዎች ሲኖሩ በቀጥታ ማጥቃትን ማስቀረት ተገቢ ነዉ:: ይህ ተገቢ የሚሆንባቸዉ ሁኔታዎች ባብዛኛዉ ሃዘኔታን ወይም አክብሮትን የሚያገኙ ሰዎች ምስክር የሆኑባቸዉ አጋጣሚዎች ናቸዉ:: እነዚህም - ህጻናት አዛዉንት የሃይማኖት ሰዎች ወይም አባቶች ወዘተ ናቸዉ:: በነዚህ አጋጣሚዎች በቂና አስተማማኝ ማስረጃ ካልኖረ በቀር እንደዚህ አይነት ሰዎችን ማፋጠጥና ማስጨነቅ በዳኞችና ሂደቱን በሚከታለዉ ህኅብረተሰብ ፊት የሚያስጸይፍ ሊሆን ስለሚችል ዉጤቱ አፍራሽ ይሆናልና ይህ አይነቱን አቀራረብ መተዉ ተገቢ ነዉ::

ምስክርን ስለማስተባበል፡- ከመስቀለኛ ጥያቄ ሂደት ጋር የማይነጣጠለዉ ይህ ምስክርን የማስተባበል ነገር በወ/መ/ህ/ሥ/ሥ/ቁ. 145 የተፈቀደ ነዉ:: ይህ ህግ ተከሳሽ የዐቃቤህግን ምስክር የሚያስተባብልበትን ሥነሥርዓት ብቻ የሚደነግግ ይመስላል:: ሆኖም በፖሊስ ጣቢያ የተሰጠ ምስክርነት ጽሁፍ ለምስክርነት ማስተባበያ ይሆን ዘንድ ከመፈቀዱ በፊት ለፍርድቤት የሚቀርበዉ በተከሳሽ ጥያቄ ብቻ ሳይሆን በዐቃቤህግም ጭምር ነዉ:: ከዚህ በኋላ ፍርድቤት ጽሁፉን ለማስተባበያነት እንዲሰጠዉ የሚያደርገዉ ለተከሳሹ ነዉ::
ያም ሆነ ይህ በተለመደዉ አሰራር መሰረት ዐቃቤህግ የራሱን ምስክር በተመለከተ ቃሉን እየለወጠ መሆኑን ለማስረዳት በፖሊስ ጣቢያ የሰጠዉን ቃል ጽሁፍ ለምስክሩ አሳይቶ ፊርማዉን እንዲያረጋግጥ ካደረገ በኋላ ለፍርድቤት በማቅረብ ሲያስወስን ይታያል:: በተመሳሳይ ሁኔታ የተከሳሹ ምስክር በፖሊስ ምርመራ ጊዜ የሰጠዉን ቃል ጽሁፍ ለማስተባበያነት እንዲታይለት ቢጠይቅ ምን ስህተት አለዉ? የተከሳሽ ምስክር በፖሊስ ጣቢያ የምስክርነት ቃል ሊያስመዘግብ ይችላል? የተከሳሽ ምስክር በወንጀል ምርመራ ጊዜ በጉዳዩ ላይ ቃሉን በምስክርነት ከሰጠ በኋላ ዐቃቤህግ ማስረጃ አድርጎ ሳይቆጥረዉ ቢቀርና ተከሳሽ ምስክሩ ቢያደርገዉ ለፖሊስ ምስክርነቱን የሰጠ ምስክር ሊባል አይችልም?
በኢትዮጵያ ህግ መሰረት የሚደረገዉ ማስተባበል ቀድሞ በተሰጠ ቃል ላይ የተመረኮዘ ነዉ:: ሆኖም የማስትባበል ስራ ቀደም ሲል በምስክሩ በተደረገ ሌላ ተግባርም ሊከናወን ይችላል:: እንዲሁም የምስክሩን ባህሪ (ምናልባትም የመዋሸት) እና በጉዳዩ ዉጤት ምስክሩ የሚኖረዉን ጥቅም በማሳየት ምስክሩን ማስተባበል ይቻላል::

ከወ/መ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 145 ዉጪ ያሉ ምስክር ማስተባበያ ዘዴዎች፡- የቀድሞ የምስክር ቃልንም በተመለከተ ህጉ በፖሊስ ጣቢያ የተመዘገበን ቃል ብቻ ይገልጻል:: ቀደም ሲል በፍርድቤት በማንኛዉም ጉዳይ የተመዘገበ ቃልስ ምስክሩን ለማስተባበል አይዉልም? የቀዳሚ ምርመራ ፍርድቤት የመዘገበዉ ምስክርነት ለዚህ አገልግሎት ማዋል አይቻልም? በክስ መስማት ጊዜ በፍርድቤት ከሚደረግ የቃል ምዝገባ ሌላ ቃልን ለመመዝገብ ብቻ በሚሰራ ፍርድቤት ቃል ሊመዘገብ አይችልም (የወ/መ/ህ/ሥ/ሥ/ቁ. 35)? ምስክሩ ባለዉ የሥራ ኃላፊነት መሰረት የጻፋቸዉ ጽሁፎች ወይም ደብዳቤዎች ምስክሩን ለማስተባበል አያገለግሉም?
በነዚህ በሁሉም ሆነ በፖሊስ ጣቢያ ቃል ምስክርን ለማስተባበል አስቀድሞ ይህን ቃል ወይም መጻጻፍ እና ይዘቱን ማወቅ እንደሚያስፈልግ አያጠያይቅም:: ለዚህ ደግሞ ከዚህ በፊት እንደተገለጸዉ ዝግጅት ማድረግ የማይታለፍ ይሆናል::
Via #Tsegaye Demeke - Lawyer
#አለ_ህግ #Ale_Hig @Lawsocieties
Commercial Code/አዲሱ ንግድ ህግ
____
Feteh’s subcontractor ARTS TV produced a “Legal Reform in 5” spotlight program to introduce the revised Commercial Code Proclamation No. 1243/2021.

Mr. Fikadu Petros, a member of the Commercial Code Drafting Team, explains the changes made in relation to the types of business organizations that can be legally established and bankruptcy.

#USAIDETHIOPIA #FetehActivityEt

https://youtu.be/llH0rw5yYQE

#አለ_ህግ #Ale_Hig @Lawsocieties
🎰 የማንዋል ደረሰኝ የሚጠቀም የታክስ ከፋይ
ኃላፊነት
ማንኛውም የማንዋል ደረሰኝ እንዲጠቀም የተፈቀደለት የታክስ ከፋይ የሚከተሉት ኃላፊነቶች ይኖሩበታል፡፡
• በባለሥልጣኑ ፈቃድ (ዕውቅና) ያልተሰጣቸውን ደረሰኞች አለመጠቀም፤
• ለአንድ ግብይት ጥቅም ላይ የዋለን ደረሰኝ ለሌላ ግብይት አለመጠቀም፤
• በበራሪና ቀሪ ቅጠሎች ላይ የተለያየ መረጃ አለመመዝገብ፤
• ግብይቱ ከተከናወነበት ሽያጭ ዋጋ የተለየ የገንዘብ መጠን በደረሰኙ ላይ አለማስፈር፤
• የደረሰኝ ህትመት ከተፈቀደለት ግብር ከፋይ ውጪ ለሌላ ታክስ ከፋይ ጥቅም ላይ እንዲውል አለማድረግ፤
• ያለደረሰኝ ሽያጭ አለማከናወን፤
• ደረሰኝ ለሚጠይቁ ግዥ ፈፃሚዎች ሽያጭ አለመከልከል፤
• ተመሳሳይ ቁጥር ያለው ደረሰኝ በማሳተም ጥቅም ላይ አለማዋል፤
• እንዲሰረዝ ውሳኔ በተሰጠበት ደረሰኝ አለመጠቀም፤
• ደረሰኝ ሲታተም ዝርዝር መረጃዎችን አሟልቶ የያዙ ደረሰኞችን አሳትሞ መጠቀም፤
• በራሪና ቀሪ ቅጠሎች ያለው ደረሰኝ ማሳተም፣ ደረሰኞችን በጥንቃቄ መያዝ እና ግብይት የተፈጸመባቸውን ደረሰኞች በታክስ አዋጁ እስከተገለፀ ጊዜ ድረስ ይዞ ማቆየት፣ ለሒሳብ ምርመራ ወይም ለግብር አወሳሰን እንዲቀርብ በሚጠየቅበት ጊዜ ማቅረብ፤
• የደረሰኝ አጠቃቀም መከታተያ ሌጀር ለሁሉም በግልጽ በሚታይበት ቦታ መስቀል እና ትክክለኛ መረጃ እንዲይዝ ማድረግ፤
#አለ_ህግ #Ale_Hig @Lawsocieties
https://t.me/lawsocieties
1238_2013 የመገናኛ ብዙሃን አዋጅ.pdf
2 MB
ይህ አዋጅ "የመገናኛ ብዙሃን አዋጅ ቁጥር ፩ሺ፪፻፴፰/፪ሺ፲፫" ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል፡፡
#አለ_ህግ #Ale_Hig @Lawsocieties
Online Media Directive_Ethiopia.pdf
292.8 KB
የበይነ-መረብ መገናኛ ብዙሃን መመሪያ
ቁጥር 902/2014

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን
ግንቦት 2014 ዓ.ም
አዲስ አበባ
#አለ_ህግ #Ale_Hig @Lawsocieties
የዓለማችን ከፍተኛ ደመወዝ ተከፋይ መሪ ማን ነው?

የሲንጋፖሩ ጠቅላይ ሚኒስትር በዓመት 2 ሚሊዮን ዶላር የሚከፈላቸው መሪ ናቸው።

https://am.al-ain.com/article/the-salary-list-of-world-leaders
የአማራ ክልል ዳኞች ማህበር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰሞኑን በፓርላማ ባደረጉት ንግግር "1ኛ ደረጃ ሌቦች ዳኞች ናቸው" በሚል በገለፁት ጉዳይ ይቅርታ እንዲጠይቁ አሳሰበ።
Investment Flows to Africa Reached a Record $83 billion in 2021

Foreign direct investment (FDI) to African countries hit a record $83 billion in 2021, according to UNCTAD’s World Investment Report 2022 published on 9 June.
#EthiopianBusinessDaily
#አለ_ህግ #Ale_Hig @Lawsocieties
በአንድ ተማሪ ላይ የድብደባ ወንጀል የፈፀሙ የፖሊስ አባላትን በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያጣራ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ!

ጉለሌ ክ/ከተማ ወረዳ 7 ሰሜን ማዘጋጃ ጋበር ሆቴል በሚባል አካባቢ ሰኔ 8 ቀን 2014 ዓ/ም ከቀኑ 5 ሰዓት ላይ በክፍል ውስጥ ርንቺት ተኩሶ ከት/ቤት ውስጥ አምልጦ የሄደ አንድ ተማሪን አራት የፖሊስ አባላት ተከታትለው በመያዝ የድብደባ ወንጀል ፈጽመውበታል፡፡

ህገ- ወጥ ድርጊቱ በማህበራዊ ሚዲያ ከተለቀቀ በኋላ ፖሊስ ባደረገው ማጣራት ድል በር 2ኛ ደረጃ በሚባል ት/ቤት የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ነው በሚል ፕሮግራም ላይ በክፍል ውስጥ በተደረገ ዝግጅት አንድ ተማሪ ርችት እንደተኮሰ እና በት/ት ቤት ውስጥ ርችት መተኮሱ ሌሎች ተማሪዎችን እንደረበሻቸው ለፖሊስ መረጃ ይደርሰዋል፡፡

በእለቱ ድርጊቱን ፈፅሟል የተባለው ተማሪ ከት/ቤቱ ቅጥር ግቢ እንደወጣ የተነገራቸው 4 የጉለሌ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ አባላት ክትትል በማድረግ ሰሜን ማዘጋጃ ጋበር የሚባል ሆቴል አካባቢ ተማሪውን ይዘውት ተገቢ ያልሆነ ድብደባ ፈፅመውበታል፡፡

የአ/አበባ ፖሊስ እንዳስታወቀው ፖሊስ መረጃው ካደርሰው በኋላ ተጠርጣሪ የፖሊስ አባላቱን በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያጣራ ይገኛል፡፡

በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ የህግ አስከባሪነት መነሻው ህግን ማክበር መሆኑን ያስታወቀው ፖሊስ የዜጎችን ህጋዊ መብት በሚፃረሩ የፖሊስ አባላት ላይ የሚወሰደውን ዕርምጃ አጠናክሮ እንደሚቀጥልና በማንኛውም ሁኔታ ህገወጥ ተግባራት ሲፈፀሙ ህ/ሰቡ በያገባኛል ስሜት የሚሰጠውን መረጃ አጠናክሮ እንዲቀጥል ፖሊስ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡ ኢትዮመረጃ