የብሔራዊ ባንክ ውሳኔ በፍርድ ቤት እንደማይሻር የሚገልጽ አንቀጽ በረቂቅ አዋጅ መካተቱ ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄ አስነሳ
👇👇👇👇👇
በባንክ ዘርፍ የውጭ ባለሀብቶች እንዲሳተፉ ተሻሽሎ በቀረበው የባንክ ሥራ ረቂቅ አዋጅ የሞግዚት አስተዳደርን በተመለከተ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ውሳኔ በማንኛውም ፍርድ ቤት ውሳኔ እንደማይሻር የሚገልጽ አንቀጽ መያዙ፣ ሕገ መንግሥታዊ መብትን የሚጋፋ ነው የሚል ጥያቄ ተነሳበት፡፡
ይህ ጥያቄ የተነሳው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀትና የፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የብሔራዊ ባንክና የባንክ ሥራ ረቂቅ አዋጆች ላይ ሰኞ ኅዳር 2 ቀን 2017 ዓ.ም. ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር የአስረጂ ውይይት ሲካሄድ ነው፡፡
በብሔራዊ ባንክ በተወሰነ የሞግዚት አስተዳደር ሹመት፣ በባንክ ፈቃድ ስረዛና በንብረት አጣሪ ሹመት ምክንያት በሚደርስ ጉዳት ለአቤቱታ አቅራቢ አካል የገንዘብ ካሳ ሊከፍል ይችላል እንጂ፣ የብሔራዊ ባንክ ውሳኔ በማንኛውም ፍርድ ቤት ወሳኔ አይሻርም የሚል አንቀጽ በረቂቅ አዋጁ ተካቶ መቅረቡ የሕጋዊነት ጥያቄ አስነስቷል፡፡
በረቂቁ ለብሔራዊ ባንክ የተሰጠው ኃላፊነት ሕገ መንግሥቱንና ለፍርድ ቤት የተሰጠውን ሥልጣን፣ እንዲሁም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 37 የተደነገገውን ፍትሕ የማግኘት መብት የሚጋፋና ድንጋጌውን የሚቃረን በመሆኑ እንዲስተካከል ቋሚ ኮሚቴው ጠይቋል፡፡ብሔራዊ ባንክ ወይም የባንኩ ዳይሬክተሮች፣ ሥራ አመራር ወይም ወሳኝ የባለቤትነት ድርሻ ያላቸው ባለአክሲዮኖች የገንዘብ አስቀማጩን ጥቅም ጉዳት ላይ ሊጥሉ የሚችሉ ድርጊቶችን ፈጽመዋል ብሎ ካመነ፣ የሞግዚት አስተዳደር ሊሾም እንደሚችል በረቂቁ ተካቷል፡፡
ረቂቁ ሕገ መንግሥታዊ መብትን ይጋፋል በማለት ቋሚ ኮሚቴው ላቀረበው አስተያየት የብሔራዊ ባንክ የባንክ ዘርፍ ዳይሬክተር አቶ ፍሬዘር አያሌው በሰጡት ምላሽ፣ መነሻው ዓለም አቀፍ ልምድ መሆኑንና አንድ ባንክ ቀውስ ውስጥ በሚገባበት ወቅት በፍጥነት መፍትሔ መስጠት ወሳኝ ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡
የአንቀጹ አስፈላጊነትም በዚህ ሒደት ውሳኔ ያገኙ ጉዳዮች በፍርድ ቤት ውሳኔ የሚቀለበሱ ከሆነ፣ በቀጥታ የገንዘብ አስቀማጩንና የሕዝቡን ጥቅም ስለሚጎዱ ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡በእያንዳንዱ ጉዳይ ቁርጥ ያለ ውሳኔ ሲተላለፍ የሚያመጣው አደጋ በዚያው ልክ እንደሚጨምር ተናግረዋል፡፡ ቀውስ የገጠመው ተቋም ወሳኝ የሚባል የፋይናንስ ተቋም ከሆነ፣ የደረሰው ኪሳራ ወደ መንግሥት እንዳይመጣ በሚል ታሳቢ ተደርጎ የተካተተ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በተመሳሳይ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ረቂቅ ማሻሻያ አዋጅ ውስጥ ባንኩ ወርቅና ብር፣ የአገር ውስጥና የውጭ ምንዛሪ ኖቶችና ሳንቲሞች ወደ አገር ውስጥ ሲያስገባ ወይም ወደ ውጭ ሲልክ የጉምሩክ ዲክላራሲዮን ለመሙላት አይገደድም ለሚለው ድንጋጌ ቋሚ ኮሚቴው ሕጋዊነቱን እንዴት መቆጣጥር ይቻላል ሲል ጥያቄ አቅርቧል፡፡
የባንኩ ገዥ አቶ ማሞ ምሕረቱ በሰጡት ምላሽ ባንኩ በንግድ ሥራ የተሰማራ ተቋም ባለመሆኑ፣ በየጊዜው ከውጭ በማስገባት በጉምሩክ ሥርዓት የሚያልፍ ዕቃ የለውም ብለዋል፡፡ ‹‹ባንኩ በዋነኝነት ከውጭ የሚያስገባው ነገር አለ ከተባለ ሁላችንም የምንጠቀምበት ገንዘብ ነው፡፡ እንደሚታወቀው እስካሁን ባለው ሁኔታ ገንዘብ የሚታተመው ከኢትዮጵያ ውጪ ነው፡፡ ምናልባት ባንኩ አሁን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ለሚያስገነባቸው አራት ቅርንጫፍ ሕንፃዎች የሚውል ዕቃ ከሆነ እንደ ማንኛውም አካል የሚከፈለውን እንከፍላለን፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡
አሠራሩ ከብሔራዊ ባንክ ቁልፍ ተግባር ጋር የተገናኘ ገንዘብ የማተምና የማሠራጨት ኃላፊነቱን የሚወጣበት፣ በኢትዮጵያም ሆነ በሌሎች አገሮች ከዚህ በፊት ሲሠራበት የቆየ መሆኑንና የጉምሩክ ክሊራንስ የማያስፈልገው ሚስጥራዊ ሥራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
#Reporter
#Ethiopian_law_by
#Daniel_Fikadu_Law_office⚖
አማራጭ የሕግ እውቀት
https://linktr.ee/alehig
Alternative legal enlightenment/ALE
Telegram👉 @MikiasMelak የሕግ ምክርና ድጋፍ፣ የተለያዩ ህጎች፤ አዋጅ፣ ደንብ፣ መመሪያ፣ #የሕግ_መረጃ
https://t.me/AleHig
መሰረታዊ የሕግ እውቀት alehig.com
👍16❤2