አለሕግAleHig ️
16.2K subscribers
2.84K photos
25 videos
1.86K files
3.56K links
ከጠበቃና የሕግ አማካሪ
አማራጭ የሕግ እውቀትና አገልግሎት
Alternative legal enlightenment & Service
Website: alehig.com
https://linktr.ee/alehig
WhatsApp👉 #+251920666595
Telegram👉 @MikiasMelak
የሕግ ምክርና ድጋፍ፣ የተለያዩ ህጎች፤ አዋጅ፣ ደንብ፣ መመሪያ፣ #የሕግ_መረጃ
Download Telegram
#የማስረጃ_ዓይነቶች_እና_ማስረጃ_ስለማያስፈልጋቸው_ፍሬ_ነገሮች
#መግቢያ

የአንድን ፍሬ-ነገር መኖር ወይም አለመኖር ማረጋገጥ የሚቻለው ማስረጃ በማቅረብ ነው፡፡
ማስረጃ በሰው ምስክሮች፣ በዘገባ፣ በሰነድ፣ ተጨባጭነት ባላቸዉ ሊታዩና ሊዳሰሱ በሚችሉ ነገሮች እና በኤግዚቢት መልክ ሊቀርብ ይቻላል፡፡ አቀራረቡም በሕግ በተደነገገው መሰረት ነው፡፡ በክርክር ሂደት ማስረጃ የማያስፈልጋቸው ጉዳዮች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ይህ ከፍሬ ነገሩ የተለየ ባህሪ ወይም የሚያከራክር ነገር ባለመኖሩ ምክንያት ማስረጃ ማቅረብ አስፈላጊ የማይሆንባቸዉ ሁኔታዎች ስላሉ ነዉ፡፡ በዚህ አጭር ጽሁፍ ስለ ማስረጃ ዓይነቶችና ማስረጃ ስለማያስፈልጋቸው ጉዳዮች እንመለከታለን፡፡
1. #የማስረጃ_ዓይነቶች
ማስረጃ የአንድን ፍሬ ነገር መኖር ወይም አለመኖር ለማረጋገጥ ወይም ለማስተባበል ከሚቻልባቸው ዘዴዎች እና ማስረዳት ከሚፈለገው ፍሬ ነገር ወይም መደምደሚያ ጋር ማስረጃው የሚኖረውን ግንኙነትን መሠረት በማድረግ በተለያዩ መንገዶች ከፋፍሎ ማየት ይቻላል፡፡
ፍሬ ነገርን ለማስረዳት ከምንጠቀምበት ዘዴ አንጻር፤
ሀ. የሰው ማስረጃ
ሰዎች በአካል ፍርድ ቤት ቀርበዉ ለችሎት መረጃ የሚሰጡበት መንገድ ሲሆን ፍሬ ነገሩን ለፍርድ ቤቱ የሚገልፁት በንግግር ወይም በምልክት ነው፡፡ ይህም የምስክርነት ቃል ይባላል፡፡ የሰው ማስረጃዎች ቀጥተኛ ምስክር፣ የአከባቢ ምስክርና የባለሞያ ምስክር ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
ለ. የሰነድ ማስረጃ
ይህ የማስረጃ ዓይነት በላዩ ላይ የተፃፈበት፣ የተሳለበት ወይም ማናቸዉም ዓይነት ምልክት የተደረገበት ሲሆን ለምሳሌ ውሎች፣ ቼኮች፣ ለፖሊስ ወይም ለፍርድ ቤት የተሰጠ የዕምነት ቃል የተመዘገበበት፣ በጽሁፍ የተገለፀ የላብራቶሪ ወይም የህክምና ምርመራ ውጤት የሰነድ ማስረጃዎች ናቸው፡፡
ሐ. ገላጭ ማስረጃ
ይህ የማስረጃ ዓይነት ፍርድ ቤት እንዲያየውና ግንዘቤ እንዲወስድበት የሚቀርብ ማስረጃ ነው፡፡ ለምሳሌ በወንጀል ድርጊት የተገኘ ንብረት ወይም ወንጀል ለመፈፀም አገልግሎት ላይ የዋለ መሣሪያ በማስረጃነት ሲቀርብ ገላጭ ማስረጃ ይባላል፡፡
 ማስረዳት ከተፈለገው ፍሬ ነገር አንጻር፤
 ቀጥተኛ የሆነ ማስረጃ
ማስረጃ ቀጥተኛ ነዉ የሚባለው አንድን በጭብጥነት የተያዘ ፍሬ ነገር ወይም የተወሰደን መደምደሚያ ትክክለኛነት በቀጥታ ለማረጋገጥ ወይም ለማስተባበል የሚቀርብ ሲሆን ነዉ፡፡ ከዚህ አንፃር ምስክር ቀርቦ በጭብጥ የተያዘው ፍሬነገር መኖሩን ወይም አለመኖሩን ራሱ በስሜት ህዋሳቱ አማካኝነት በማየት፣ በማሽተት፣ በመቅመስ፣ በመስማት ወይም በመዳሰስ ያወቀ መሆኑን የሚመሰክር ሲሆን ቀጥተኛ ማስረጃ ይባላል፡፡ በሰነድ ማስረጃ በኩልም በማስረጃነት የቀረበው ሰነድ በጭብጥ የተያዘዉ ፍሬ ነገር መኖርን ወይም የተደረሰበት መደምደሚያ ትክክለኛ መሆኑን ሰነዱ ራሱ በቀጥታ ያረጋግጣል ወይም ያስተባብላል በሚል የቀረበ ከሆነ ቀጥተኛ ማስረጃ ይባላል፡፡ ለምሳሌ በቂ ስንቅ ሳይኖረው ቼክ ፈርሞ ሰጥቷል በሚል ገንዘብ እንዲከፍል በተከሳሽ ላይ ለቀረበ ክስ ከሳሽ ቼኩን በማስረጃነት ያቀረበ ቢሆን ተከሳሹ ስለመፈረም አለመፈረሙ እና ስለ ገንዘቡ ልክ ቼኩ በቀጥታ የሚናገር ስለሆነ ቀጥተኛ ማስረጃ ይባላል፡፡
 ቀጥተኛ ያልሆነ ማስረጃ
ማስረጃ ቀጥተኛ ያልሆነ ነዉ የሚባለው ከሁለት ሁኔታዎች አንፃር ነዉ፡- አንደኛዉ ማስረጃ ያስረዳል የተባለዉን ፍሬ ነገር ምንጭ ማስረጃዉ ራሱ በቀጥታ ያወቀዉ ሳይሆን ከሌላ ያገኘዉ ወይም የተረዳዉ ሲሆን ነዉ፡፡ ምስክር ሌላ ሰዉ የገለፀለት መሆኑን ጠቅሶ የሚመሰክር ሲሆን ቀጥተኛ ሳይሆን የስሚ ስሚ ማስረጃ (Hearsay Evidence) ይባላል፡፡ የስሚስሚ ማስረጃን ቀጥተኛ ያልሆነ የሚያሰኘዉ ማስረጃዉ ፍሬ ነገሩን የሚገልፀዉ ራሱ በቀጥታ እንዳወቀ ሳይሆን ከሌላ ሰዉ የሰማዉ ወይም ከሰነድ ያነበበዉ በመሆኑ ነዉ፡፡ በሰነድ ማስረጃም በኩል የስሚ ስሚ የሚያሰኘዉ ማስረጃ ሆኖ የቀረበዉ ሰነድ ላይ የተገለፀዉ ፍሬ ነገር አዉቃለሁ በሚል በሌላ ሰዉ የተዘጋጀ ሲሆን ነዉ፡፡
ሁለተኛዉ ቀጥተኛ ያልሆነ ማስረጃ ነዉ የሚባልበት ሁኔታ የሚያጋጥመዉ አካባቢያዊ ማስረጃ (Circumstantial Evidence) የቀረበ እንደሆነ ነዉ፡፡ አካባቢያዊ ማስረጃ በጭብጥ ስለተያዘዉ ፍሬ ነገር መኖር አለመኖር በቀጥታ አይነግረንም፡፡ ይልቁንም የተወሰኑ ፍሬ ነገሮችን መኖር ወይም አለመኖር በማረጋገጥ ከዚህ ተነስተን በጭብጥ የተያዘዉን ፍሬ ነገር በተመለከተ አንድ ዓይነት መደምደሚያ ላይ እንድንደርስ የሚያደርግ ነዉ፡፡
የማስረጃዉ ቀጥተኛ ወይም አካባቢያዊ መሆን አለመሆኑን መለየት በማስረጃ ምዘና ጊዜ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለዉ፡፡
1. ማስረጃ ስለማያስፈልጋቸዉ ፍሬ ነገሮች
ከፍሬ ነገሮቹ የተለየ ባህሪ ወይም የሚያከራክር ነገር ባለመኖሩ ምክንያት ማስረጃ ማቅረብ አስፈላጊ የማይሆንባቸዉ ሁኔታዎች አሉ፡፡ እነሱም፡-
ሀ. ፍርድ ቤት ግንዛቤ ሊወስድባቸዉ የሚችሉ ወይም የሚገቡ ፍሬ ነገሮች፣ ለምሳሌ በአዋጅ ቁጥር 3/1987 መሠረት በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ላይ የወጡ ነገሮችን ፍርድ ቤቶች ሊቀበሏቸዉ እንደሚገባ ተደንግጓል፡፡ በነጋሪት ጋዜጣ ላይ የተገለፀ ፍሬ ነገር ለማረጋገጥ ሌላ ማስረጃ መቀበል አያስፈልግም፡፡ ጋዜጣዉን በመመልከት ብቻ ግንዛቤ ሊወሰድበት ይገባል፡፡
ለ. በፍርድ ቤት በሚደረግ የክርክር ሂደት በተከራካሪ ወገን የታመኑ ፍሬ ነገሮች
ሐ. ጠቅላላ እዉነታዎች (Universal Truth)፣
መ. የሕግ ግምቶች (Presumptions) ናቸዉ፡፡ ለምሳሌ በጋብቻ ውስጥ የተፀነሰ (የተወለደ) ልጅ አባቱ ባልየው እንደሆነ ህጉ ግምት ይወስዳል፡፡
በአጠቃላይ ግራ ቀኝ ተከራካሪ ወገኖች ያስረዱልናል የሚሏቸዉን ማስረጃዎች ወይም ማስረጃ ባይቀርብባቸዉም በሕግ መሠረት የሚወሰኑትን ለይቶ ለማቅረብ የማስረጃ ዓይነቶችን እና ማሰረጃ የማያስፈለጋቸዉን ፍሬነገሮች ማወቁ ተገቢ ነዉ፡፡
https://t.me/lawsocieties
ምንጭ፡- FDRE Ministry of Justice/ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር (13/01/2015 E.C)