የ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ጽሑፎች በPDF እና በድምጽ
2.15K subscribers
51 photos
2 videos
26 files
54 links
እዚህ ቻናል ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እምነት የሚያንጸባርቁ ጽሑፎች ይለቀቃሉ
Download Telegram
#ዕረፍተ_ቅዱሳን

† እንኳን ለብፁህ አባታችን ለአቡነ ተክለሃይማኖት በዓለ ዕረፍት በሰላም አደረሳችሁ።

ቅዱሳን ከዚህ ዓለም በሥጋ ሲለዩ አረፉ ይባላል። ሞታቸው ዕረፍታቸው ነውና። ስለ ቅዱሳን ዕረፍት ከማየታችን በፊት ሞትን በ3 ከፍሎ ማየት ተገቢ ነው።

የሥጋ ሞት: ይህ ሞት ሥጋ ከነፍስ ሲለይ ሥጋ ሞተ ያሰኘዋል። ያዕ 2:26 "ከነፍስ የተለየች ሥጋ የሞተች እንደሆነች እንዲሁ ደግሞ ከስራ የተለየ ዕምነትም የሞተ ነው።" እንዲል።

የቁም ሞት: ይህ ሞት በቁም ሳሉ እየሄዱ እየቆሙ እየተቀመጡ እየተኙ እየበሉ እየጠጡ ሥጋ ከነፍስ ሳትለይ ነገር ግን በኃጢአት ተዘፍቆ ከእግዚአብሔር መለየት ከምግባር መጉደል ከሃይማኖት በአፋ መሆን የቁም ሞት ይባላል። 1ጢሞ 5:6 "ቅምጥሊቱ ግን በህይወት ሳለች የሞተች ናት።" ብሎ ሐዋርያው በመልዕክቱ አስፍሮታል።

የነፍስ ሞት: ይህ ሞት በቁም ሳሉ በሰሩት ኃጢአት እንደቆሸሹ በንስሃ ሳሙና ሳይታጠቡ የሥጋ ሞት መቶባቸው በርደተ መቃብር ላይ ርደተ ሲኦል በነፍስ ላይ ሲፈረድባት የነፍስ ሞት ይባላል።

† የቅዱሳን ሞታቸው ግን ለእነርሱ ዕረፍታቸው ስለሆነ ቅዱሳን ሞቱ አይባልም። ይህም እንደ ምንድን ነው ቢሉ?

1 የሥጋ ሞት ቅዱሳን በዚህ ዓለም ሳሉ ካደረጉት ተጋድሎ ህማምና መከራ ወደ ዘላለማዊ ደስታ ዕረፍት መንግስተ ሰማይ ወደፈጠሪያቸው የሚሄዱበት መንገድ ስለሆነ ነው። ፊሊ 1:23 "ልሄድ ከክርስቶስ ጋር እኖር ዘንድ እናፍቃለው።" እንዳለ ሐዋርያውቅዱስ ዻውሎስ።

2 የቅዱሳን ሞት በእግዚአብሔር ዘንድ የከበረ ስለሆነ ነው። መዝ 115(116):15 "የቅዱሳኑ ሞት በእግዚአብሔር ፊት የከበረ ነው።" እንዲል።

3 ቅዱሳን በስጋ ሞት ተወስደው ወደ አምላካቸው ከሄዱ በኋላ ዕውቀታቸው ምሉዕ ስለሆነ የቅዱሳኑ ሞት ዕረፍት ይባላል። የቅዱሳን ክብርና ዕውቀት፣ ዕውቀት ሰጭ ከሆነ ከእግዚአብሔር በተሰጣቸው ጸጋ ሁሉን ያውቃሉ፡፡ ለምሳሌ ኤልሳዕ ነቢይ በዚህ ዓለም በነበረ ጊዜ ደቀ መዝሙሩ ግያዝ በምሥጢር /በስውር/ ከሶሪያዊው ንዕማን ስጦታ መቀበሉን ማንም ሳይነግረው እንዴት እንዳወቀ በሁለተኛው መጽሐፈ ነገሥት. 5፡25-27 መመልከት ይቻላል፡፡ ሌላም ከሶርያ ንጉሥ ባለሟሎች አንዱ ለንጉሡ ስለ ኤልሳዕ እንዲህ ሲል ነገር ሠራ "ጌታ ሆይ እንዲህ አይደለም ነገር ግን በእልፍኝህ ውስጥ ሆነህ የምትናገረውን በእሥራኤል ዘንድ ያለ ነቢይ ኤልሳዕ ለእስራኤል ንጉስ ይነግረዋል።" በማለት ኤልሳዕ በቦታም አንድ አካባቢ ሳይሆኑ በጸጋ መንፈስ ቅዱስ ያውቅ እንደ ነበረ ተጽፎአል። 2ኛነገ. 6፡12 በረሀብ ጊዜም የእስራኤል ንጉሥ ሊያስገድለው መልእክተኛ መላኩን ኤልሳዕ አወቀ። 2ኛነገ.6፡12 በዚህም ዓይነት ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ የሐናንያንና የሰጲራን ምሥጢራዊ ተንኮል የነገረው ሳይኖር አውቆ በሞት ቀጣቸው። የሐዋ. 5፡3-9 ታዲያ ቅዱሳን ካረፉ በኋላ ይህ ዕውቀታቸው አይለያቸውም ይልቁኑ በምድር የነበራቸው ከፊል ዕውቀት ምሉዕ ይሆናሉ። በነፍሳቸው ሕያዋን እንጂ ሟቾች አይደሉምና ነው፡፡ ለዚህም ነው ጌታ ከሰዱቃውያን ጋር ስለሙታን ይነጋገር በነበረበት ጊዜ እግዚአብሔር የአብርሃም የይስሐቅ አምላክ ነው ሲባል እነዚህ የቀድሞ አባቶች በነፍስ ሕያዋን ስለሆኑ ነው እንጂ እርሱ የሙታን አምላክ ስለሆነ አይደለም ያለው ለዚህ ነው። ማቴ 22:31-32
እስኪ ቅዱሳን እውቀታቸው በአጸደ ነፍስ ምሉዕ እንደሆነ የሚያመለክት የተወሰኑ ማስረጃዎችን እንመልከት።
ኤር 15 :1–4 "እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ ሙሴና ሳሙኤል በፊቴ ቢቆሙ እንኳ ልቤ ወደዚህ ሕዝብ አይመለስምና ከፊቴ አስወግዳቸው ይሂዱ።" ይህ አባባል የሚያመለክተው ከኤርምያስ ዘመን በፊት ከሞቱ ብዙ ዓመታት ያሳለፉት ሙሴና ሳሙኤል እስራኤል ዘሥጋ የበደሉትን ያውቁ ስለነበር እግዚአብሔርን ይማጸኑና ይማልዱ እንደነበር ነው የሚያሳየው፡፡
ሉቃ 16:19–30 በዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ አብርሃም በገነት ሆኖ በምድር ባለፀጋው ነዌ በድሀው አላዛር ላይ ያደረገበትን አውቆ አላዛርንም በእቅፉ እንዳኖረው ይናገራል። ስለዚህ የቅዱሳን ዕውቀት በአፀደ ነፍስ ምሉዕ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይመሰክራል።
4 ሞት ለቅዱሳን እንደ እንቅልፍ በመሆኑ ቅዱሳን አረፉ እንጂ ሞቱ አይባልም። ሰው በዚህ ዓለም ሳለ ከሥጋ ድካም በእንቅልፍ እንደሚያርፍ እንዲሁ ቅዱሳንም በዚህ ዓለም ሳሉ ካደረጉት ተጋድሎና መከራ በስጋ ሞት ያርፋሉና ነው። ሐዋ 7:59–60 ላይ ቀዳሜ ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስን በድንጋይ ሲወግሩት "ጌታ ሆይ ይህንን ኃጥያት አትቁጠርባቸው ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ ይህንንም ብሎ አንቀላፋ።" እንዲል።

5 ቅዱሳን በዕረፍታቸው ክብራቸው ይገለጣል።ልዑል እግዚአብሔርም ቃልኪዳን ይገባላቸዋል። መዝ 88:2 "ከመረጥኳቸው ጋር ቃልኪዳኔን አደረግኹ።" እንዳለ በዕለተ ዕረፍታቸው ቃልኪዳንን ከፈጣሪያቸው ይቀበላሉ።
ከቅዱሳን ረድኤት በረከት ይክፈለን። የጻድቁ አባት የአቡነ ተክለሃይማኖት ምልጃ አይለየን። የእመቤታችን ፍቅሯ በልባችን ጣዕሟም በአንደበታችን ይኑር። ይቆየን።

#ከወንድማችን አቤኔዘር (ወልደ ተክለሃይማኖት)