አለሕግAleHig ️
16.2K subscribers
2.83K photos
25 videos
1.86K files
3.56K links
ከጠበቃና የሕግ አማካሪ
አማራጭ የሕግ እውቀትና አገልግሎት
Alternative legal enlightenment & Service
Website: alehig.com
https://linktr.ee/alehig
WhatsApp👉 #+251920666595
Telegram👉 @MikiasMelak
የሕግ ምክርና ድጋፍ፣ የተለያዩ ህጎች፤ አዋጅ፣ ደንብ፣ መመሪያ፣ #የሕግ_መረጃ
Download Telegram
ሰ/መ/ቁጥር 241073 ሀምሌ 27 ቀን 2015 ዓ/ም #ውርስ_ህግ #ኑዛዜ
አመልካች፡- አቶ ዳዊት አበራ አቶ ዳዊት አበራ- ሞግዚት ፀሐይነሽ ተሾመ 
ተጠሪ፡- ወ/ሮ አለምነሽ ከፈለኝ-
በሁኔታ ላይ የተመሰረተ (conditional legaty) ወይም በገደብ የተደረገ ኑዛዜ

በ#ወራሽ የገቢ ማጣት እና በጤና ሁኔታ ችግር የተነሳ ኑዛዜ ሊሻሻል ወይም ቀሪ ሊሆን ስለሚችልበት ሁኔታ
#ፍ/ሕ/ቁጥር 879/1 እና #ፍ/ሕ/ቁጥር 872

በዚህ መዝገብ አመልካች የሟች ልጅ ሲሆኑ ተጠሪ ሟች ኋላ ላይ (ከአመልካች እናት በኋላ) ያገቧት ሚስት ናት። ሟች ለልጆቻቸው ንብረታቸውን እንዲወርሱ ኑዛዜ የተዉ ቢሆንም በኑዛዜው ተጠሪ በህይወት እስካሉ የመጠቀም መብት የተሰጣቸው በመሆኑ ኑዛዜው ተፈጻሚነት የሚያገኘው ተጠሪ ከሞቱ በኋላ ነው።
የአመልካች ጥያቄ ሟች ለተጠሪ በውርስ ሐብት በህይወት እስካሉ እንዲጠቀሙ ኑዛዜ ማድረጋቸው አመልካች ያለብኝን የአይምሮ ጤና እና የኑሮ ችግር ለመወጣት እንዳልችል የሚያደርገኝ ስለሆነ (በተጨማሪም ኑዛዜው በዝምታ የነቀለኝ ስለሆነ የሚል መከራከሪያም አቅርበዋል።) ኑዛዜው ሊፈርስ ይገባል የሚል ነው።

የ#ሰበር ችሎቱ የተያዘውን ጉዳይ አስመልክቶ የሰጠው ውሳኔ እና የሐተታው ክፍል ከዚህ በታች ይነበባል

አመልካች ባለባቸው ጤና ችግር ምክንያት ስራዎችን በመስራት ወይም በሌላ በማናቸውም ምክንያት የራሳቸውን ገቢ ማግኘት እና ለኑሮ አስፈላጊ የሆኑ ወጪዎችን መሸፈን የማይችሉ መሆኑ የተረጋገጠ ሲሆን ሟች ለክርክሩ መሰረት በሆነው ኑዛዜ ለተጠሪ በህይወት እስካሉ በውርስ ሀብቱ የመጠቀም መብት ባያስተላልፉ ኖሮ አመልካች የውርስ ድርሻውን በማግኘት ለኑሮ እና ለጤና አስፈላጊ የሆኑ ወጪዎችን ለመሸፈን ያስችላቸዋል፡፡ የሟችን ፍላጎት ለማስጠበቅ ሲባል ብቻ የአመልካች የከፋ ችግር እየታወቀ በኑዛዜ የተቀመጠው ገደብ መቀጠል አለበት የሚባል ከሆነ የአመልካችን በህይወት የመኖር መብት አደጋ ላይ የሚጥል በመሆኑ ለሞራል ተቃራኒ ይሆናል፡፡ ተጠሪ በሰጡት መልስ የአመልካች ብቻ ሳይሆን የተጠሪም የጤና ችግር ከግምት ሊገባ ይገባል በሚል የሚከራከሩ ቢሆንም ተጠሪ ለክርክር መሰረት ከሆነው ንብረት ላይ 50% የሚስትነት ድርሻ ያላቸው ከመሆኑ አንጻር በኑዛዜው ላይ የተቀመጠው ገደብ አመልካችን በተመለከተ ብቻ ተፈጻሚነቱ ቢቀር በተጠሪ ላይ የሚደርስባቸው ጉዳት ከፍተኛ ወይም ለሞራል ተቃራኒ ነው ሊባል አይችልም፡፡

ሟች ለተጠሪ በህይወት እስካሉ የውርስ ድርሻቸውን የመጠቀም መብት በኑዛዜ አስተላልፈዋል፡፡ በኑዛዜው መሰረት የሟች ወራሾች ድርሻቸውን ማግኘት የሚችሉት ተጠሪ ከዚህ አለም በሞት ሲለዩ ብቻ ነው፡፡ ይህም ሟች ለወራሾቻቸው ያረጉት ኑዛዜ በሁኔታ ላይ የተመሰረተ (conditional legaty) ወይም በገደብ የተደረገ ኑዛዜ መሆኑን ያሳያል፡፡ በኑዛዜ የተጠቀሰው ሁኔታ ወይም በወራሾች ላይ በኑዛዜ የተደረገው ገደብ እንዳልተደረገ ሊቆጠር የሚችለው ግዴታው የማይቻል ወይም ለህግ ወይም ለመልካም ጠባይ ወይም ለሞራል ተቃራኒ ሆኖ ሲገኝ መሆኑን በፍ/ሕ/ቁጥር 879/1 ስር ተመልክቷል፡፡ በተጨማሪም በፍ/ሕ/ቁጥር 872 ስር ሟቹ በፊት ካደረገው ጋብቻ የተገኙ ተወላጆች ያሉት ከሆነ ለኋላኛው ባል ወይም ሚስት ጥቅም የተደረገ የኑዛዜ ቃል በዳኞች ሊቀነስ ወይም ሊሻር እንደሚችል ተመልከልቷል፡፡

እነዚህ ሁለት ድንጋጌዎች ሟች ከቀድሞ ትዳር የተፈሩ ልጆች እያሉ ለኋላኛው ሚስት ወይም ባል የተደረገ ኑዛዜ ከቀድሞ ትዳር የተወለዱትን ልጆች ጥቅም የሚጎዳ ከሆነ በተወላጆቹ ጠያቂነት ዳኞች ኑዛዜውን ለማሻሻል ወይም ሙሉ ለሙሉ ቀሪ ሊያደርጉ እንደሚችሉ፤ በተለይም ኑዛዜው በግዴታ ላይ የተመሰረተ ከሆነ እና ግዴታው ለህግ፣ ለሞራል ወይም ለመልካም ጠባይ ተቃራኒ ከሆነ በኑዛዜው የተመለከተው ገደብ ወይም ግዴታ በኑዛዜው እንዳልተጻፈ ይቆጠራል፡፡ በእርግጥ እነዚህ ድንጋጌዎች ተግባራዊ ሲደረጉ በጥንቃቄ ሊሆን ይገባል፡፡ ምክንያቱም ኑዛዜ የተናዛዙን ፍላጎት መግለጫ እና ሟች ንብረቱን ለሚፈልገው ሰው የማስተላለፍበት አንዱ መንገድ በመሆኑ ኑዛዜው ሲቀነስ ወይም ሲሻሻል ወይም በኑዛዜ የተቀመጠው ገደብ እና ግዴታ ቀሪ ሲደረግ የተናዛዙን ፍላጎት እንዳይቃረን መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ በሌላ በኩል ኑዛዜው ላይ የተገለጸው ግዴታ ለመፈጸም የማይቻል ወይም ለህግ ወይም ለሞራል ወይም ለመልካም ጠባይ ተቃራኒ መሆኑ በጥንቃቄ በዳኞች ተመርምሮ ግዴታው ሊፈጸም የማይችል ወይም ለህግ ወይም ለሞራል ወይም ለመልካም ጠባይ ተቃራኒ ሆኖ ከተገኘ በኑዛዜ ላይ የተመለከተው ገደብ ወይም ግዴታ ቀሪ ሊሆን ይገባል፡፡