አለሕግAleHig ️
16.2K subscribers
2.84K photos
25 videos
1.86K files
3.56K links
ከጠበቃና የሕግ አማካሪ
አማራጭ የሕግ እውቀትና አገልግሎት
Alternative legal enlightenment & Service
Website: alehig.com
https://linktr.ee/alehig
WhatsApp👉 #+251920666595
Telegram👉 @MikiasMelak
የሕግ ምክርና ድጋፍ፣ የተለያዩ ህጎች፤ አዋጅ፣ ደንብ፣ መመሪያ፣ #የሕግ_መረጃ
Download Telegram
........Rewrting ........, [07.10.19 09:42]
የፌደራል ጠቅላይ ዕቃቤ ሕግ
የመጀመሪያ ደረጃ የክስ መቃወሚያ (preliminary objection) ሲባል ምን ማለት ነው?
______________________
ሰላም እንዴት ናችሁ ውድ የፌስቡክ ገጻችን ተከታታዮች ብዙውን ጊዜ በዜና አውታሮች ፍርድ ቤቱ በነ እገሌ የክስ ሂደት ላይ የመጀመሪያ ደረጃ የክስ መቃወሚያ ለመስማት ቀጠሮ ሰጠ ሲባል እንሰማለን ለመሆኑ የመጀመሪያ ደረጃ የክስ መቃወሚያ ሲባል ምን ማለት ነው? ለዛሬ በዚሁ አርዕሰት ላይ እናንተን ያስተምራል ያልነውን ጥንቅር ወደናንተ ልናደርስ ወደድን ተከታተሉን፡፡
የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ማለት ተከሳሹ ስለ ክሱ ማመልከቻ ፎርም ወይም በክስ ማመልከቻ የተገለፀውን ነገር የሚቃወምበት ስርዓት ነው፡፡የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ አላማ ፍርድ ቤት እና ተከራካሪ ወገኖች ወደ ክርክሩ ፍሬ ነገር ሳይገቡ መነሳት ያለባቸውን ነጥቦች በማንሳት ውሳኔ በመስጠት ጊዜ መቆጠብ ነው፡፡ በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ ውስጥ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ሊነሳባቸው የሚችሉ ነጥቦች በዝርዝር ተቀምጠዋል፡፡
የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ የክሱን ይዘት በተመለከተ ሊቀርብ ይችላል፡፡ይህም ማንኛውም የክስ ማመልከቻ ቀንና ዓመተ ምህረት የተፃፈበት እና የተፈረመበት እንዲሁም ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን እንዲገልፅ ያስፈልጋል፡፡እነዚህም ተከሳሽ የተከሰሰበት ወንጀል እንዲሁም የወንጀሉ መሰረታዊ ነገር እና ሁኔታዎች፤ወንጀሉ የተፈፀመበት ጊዜ እና ስፍራ ተገቢ በሆነ ጊዜም በደል የደረሰበት ሰው ስም ወይም ወንጀሉ የተፈፀመበት ንብረት፣ተከሳሽ ድርጊቱን በመፈፀም የተላለፈው የህግ አንቀጽ መያዝ አለበት፡፡ክሱ ግልፅ እና የተከሳሽን የመከላከል መብት የማያጣብብ መሆን አለበት፡፡
በመሆኑም እነዚህ ነገሮች ግልፅ ባልሆኑ እና ባልተሟሉ ጊዜ ተከሳሽ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ማንሳት ይችላል፡፡ በተጨማሪ በወ/መ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 130/2 ስር የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ የሚያስነሱ ነገሮች ተዘርዝረው ይገኛሉ፡፡
• ተከሳሽ በዚሁ ነገር ክስ በሌላ ፍርድ ቤት ተጀምሮ በቀጠሮ ያለ መሆኑ
• በዚሁ ክስ ከዚህ በፊት ተከሶ ነፃ የወጣ ወይም የጥፋተኝነት ውሳኔ የተሰጠበት መሆኑ
• ክስ የቀረበበት ወንጀል በይርጋ ህግ የታገደ ወይም ምህረት ወይም ይቅርታ የተደረገለት መሆኑ ከተረጋገጠ፡፡ ይርጋ ማለት አንድ የወንጀል ድርጊት ተፈፅሞ ክስ ለማቅረብ በ1996 ዓ.ም በወጣው የወንጀል ህግ የተቀመጠው የጊዜ ገደብ ማለት ነው፡፡በወንጀል ህግ አንቀጽ 219 ስር እንደተደነገገው የይርጋ ዘመን የሚታሰበው የቅጣት ማከበጃ ወይም ማቅለያ ሁኔታዎች ግምት ውሰጥ ሳይገቡ በወንጀል ህጉ ልዩ ክፍል የተደነገገው ከፍተኛ ቅጣት መሰረት በማድረግ ነው፡፡የይርጋ ዘመኑ መቆጠር የሚጀምረው ጥፋተኛው የወንጀል ድርጊቱን ከፈፀመበት አንስቶ ነው፡፡ለምሳሌ ከአምስት ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራት የሚያስቀጣ ወንጀል ወንጀሉ በተፈፀመ በአስር አመት ውስጥ ክስ መቅረብ አለበት፡፡አስር አመት ካለፈ ግን ክስ ማቅረብ አይቻልም ማለት ነው፡፡
• ከሌሎች ወንጀለኞች ጋር በተከሰሰ ጊዜ እና ለብቻው ተነጥሎ ክሱ ባይታይለት የሚጎደው መሆኑን፣
• ክሱን ለማቅረብ በህጉ መሰረት ፈቃድ ያልተሰጠ መሆኑ ለምሳሌ ተከሳሽ በአለም አቀፍ ህግ ዲፕሎማቲክ ኢሙኒቲ የማይከሰስ እንደሆነ፣
• በሌላው ችሎት የቀረበው ክስ ሳይፈፀም በዚህ የወንጀል ክስ ሊሰጥ የማይገባ መሆኑ፣
• ለፈፀማቸው ተግባሮች ኀላፊ አለመሆን ፤ለምሳሌ የተከሳሽ አድሜ ከዘጠኝ አመት በታች ከሆነ፣ በወንጀል ህግ አንቀጽ 48 ላይ እንደተመለከተው ማንም ሰው በእድሜ ፣ በህመም ፣ባልታሰበ የእድገት መዘግየት ወይም ጥልቅ በሆነ የአዕምሮ የመገንዘብ ችሎታ መቃወስ ወይም የወንጀል ድርጊት በሚፈፅምበት ጊዜ የድርጊቱን አይነት ወይም ውጤት ለመገንዘብ ወይም በዚህ ግንዛቤ መሰረት ራሱን ለመቆጣጠር በፍፁም ያልቻለ ሲሆን ኢ-ኃላፊ ስለሚሆን አይቀጣም፡፡
ከላይ የተዘረሩት ነጥቦች ባጋጠሙ ጊዜ ተከሳሽ እራሱ ወይም ጠበቃ ካለው በጠበቃው አማካኝነት በመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያነት ሊያነሳ ይችላል፡፡
ነገር ግን ፍርድ ቤቱ ሲጠይቀው ተከሳሹ የክሱን ማመልከቻ ወዲያውኑ ካልተቃወመ በቀር ቆይቶ እንዲህ ያለውን መቃወሚያ ነገሩ በሚሰማበት በሌላ ጊዜ ሊነሳ የሚችለው ፍርድ ቤቱን የሚፀና ፍርድ ለመስጠት የሚያግደው ከሆነ ብቻ ነው (ወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.130/3)፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ ተከሳሽ አንድ ጊዜ ተከሶ በተቀጣበት ወንጀል ድጋሚ ሊከሰስ እንደማይገባ ይህም በመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያነት ባይነሳም በማንኛውም ጊዜ ሊነሳ እንደሚችል የሚያሳየንን የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰ/መ/ቁ 72304 የሰጠውን ውሳኔ እንደ አብነት ማየት አስፈላጊ ነው፡፡
ጉዳዩ ባጭሩ ተከሳሽ በስር ፍርድ ቤት በቀላል አካል ጉዳት ማድረስ ወንጀል ተከሶ ከተቀጣ በኃላ ተበዳይ በመሞታቸው ዐቃቤ ህግ ድጋሚ በቸልተኝነት ሰው መግደል ወንጀል ክስ ሲያቀርብ ተከሳሽ እንደ መጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ሳያነሳ ቀርቶ በኃላ በተመሳሳይ ወንጀል ድጋሜ ያለመከሰስ መብት principle of double jeopardy ይነካል ማለቱ ተገቢ አይደለም ብሎ የተከራከረበት ጉደይ ነው፡፡
ሰበር በውሳኔ ዝርዘሩ ላይ እንዳስቀመጠው “ አንድ ሰው በወንጀል ህግ እና ስነ ስርዓት ተከሶ የመጨረሻ ፍርድ በተሰጠበት ጉዳይ ጥፋተኛ ሆኖ ተቀጥቷል ወይም ነፃ ተለቋል የሚለው መከራከሪያ በመጀመሪያ የወንጀል ክስ የክስ መቃወሚያ ሆኖ መቅረብ ያለበት መሆኑ በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 130 የተደነገገ ሲሆን ፍርድ ቤቱ የቀረበው የክስ መቃወሚያና ማስረጃ በመመርመር ውሳኔ መስጠት ያለበት መሆኑ በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 131 ተደንግጓል፡፡ሆኖም አንድ ተከሳሽ በወንጀል ተከሶ በመጨረሻ ፍርድ በነፃ በተለቀቀበት ወይም በተቀጣበት የወንጀል ድርጊት በድጋሜ ያለመከሰስ ያለመጠየቅ መብት መሰረታዊ እና ህገ መንግስታዊ መብት በመሆኑ ክርክሩ በሚካሄድበት በማናቸውም ደረጃ ሊነሳ የሚችልና በማስረጃ ተረጋግጦ በተገኘ ጊዜ ፍርድ ቤቶች ተቀብለው ብይን ሊሰጡበት የሚገባ መሆኑ በውሳኔው አስፍሯል፡፡
ከመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ጋር ሊምታታ የማይገባው መቃወሚያ በማለት ተከራካሪ ወገኖች እንደ አስፈላጊነቱ ዐቃቤ ሕግም ይሁን ተከሳሽ በክርክር ወይም ምስክር በሚሰማበት ጊዜ ጣልቃ የሚገቡበት ስነ ሥርዓት ነው፡፡
ለምሳሌ ምስክር በሚሰማበት ጊዜ ለምስክሩ በዋና ጥያቄ ላይ መሪ ጥያቄ ቢቀርብ ወይም ምስክሩ ከተመለከተው ወይም ከሚያውቀው ነገር ባሻገር ግላዊ አስተያየቱን ወይም ግምቱን እንዲሰጥ ቢጠየቅ ወይም ከጉዳዩ ጋር የማይገናኝ ጥያቄ ቢጠየቅ ተከራካሪ ወገኖች መቃወሚያ አለኝ ብለው ፍርድ ቤቱን በማስፈቀድ ምስክሩ መልስ እንዳይመልስ ማድረግ ይችላሉ፡፡
ውድ አንባቢያን ለዛሬ ካዘጋጀንላችሁ ጥንቀር በጉዳዩ ዙሪያ ዕውቀት እንደጨበጣችሁ ተስፋ እናደርጋለን በቀጣይ በሌላ ፕሮግራም እስክንገናኝ መልካሙን ሁሉ ተመኝን ሰላም፡፡ https://t.me/lawsocieties
እንደዋዛ!
ሰላም እንዴት ናችሁ ውድ የኢፌድሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የፌስቡክ ገጽ ተከታዮቻችን "እንደዋዛ" በተሰኘው ፕሮግራማችን ብዙውን ጊዜ ችላ የምንላቸው፤ ነገር ግን ወንጀል ሆነው በህግ ማህደሮቻችን ላይ ሊያስጠይቁ እንደሚችሉ የተቀመጡ ጉዳዮችን የምናይበት ፕሮግራም ነው፡፡

ለዛሬ ያከራዩትን ሰው ማንነት አለማሳወቅ ከ3 እስከ 10 ዓመት ጽኑ እሥራት እንደሚያስቀጣ ያውቃሉ? በሚል አርዕስት ላይ ተከታዩን አጭር ጹሁፍ ልናስነብባችሁ ወደናል መልካም ንባብ፡፡ ማንኛውንም ቤት፣ ለንግድ ቢሆን ለመኖሪያ፣ ቦታ፣ ክፍል ወይም ተሽከርካሪ የሚያከራዩ ከሆነ ይህንን የሕጉን አንቀጽ ከግምት ያስገቡ፡፡

በ2001 ዓ.ም የወጣው የጸረ-ሽብር አዋጅ አዋጅ ቁጥር 652/2001 በአንቀጽ 15 ማንኛውም ቤት፣ ቦታ፣ ክፍል ወይም ተሽከርካሪ ወይም ተመሳሳይ መገልገያ አከራይ (ልብ ይበሉ አከራይ) የሆነ ሰው የተከራዩን ማንነት በዝርዝርና በጽሑፍ የመያዝ እንዲሁም በአቅራቢያው ላለ ፖሊስ ጣቢያ በሃያ አራት ሰዓት ውስጥ የማሳወቅ ግዴታ አለበት ብሎ ደንግጓል፡፡

በዚህም መሠረት አከራይ ከሆኑ የሚያከራዩትን ሰው ማንነት ማለትም ስም፣ አደራሻ እንዲሁም መታወቂያ ወይም ፓስፖርት ወይም ማንኛውም ዓይነት ማንነትን የሚገልጽ ማስረጃ ኮፒ በማድረግ በአቅራቢያዎ ወደሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ በሃያ አራት ሰዓት ውስጥ በመሔድ የማሳወቅ ግዴታ አለበዎት፡፡
በተለይ የቤት ኪራይ በመኖሪያ ቤትዎ እያከራዩ ከሆነና ያከራዩት ሰው ማንነት የውጭ ሀገር ዜግነት ያለው ከሆነ የፓስፖርቱን ቅጂ የመያዝና ለፖሊስ የማቅረብ ግዴታ ያለበዎት መሆኑን ይኼው አዋጅ በአንቀጽ 15 ንዑስ አንቀጽ 2 ሥር ደንግጓል፡፡ ይህንን ግዴታ ያልተወጡ እንደሆነ ማለትም አከራይተው ስለአከራዩት ሰው ማንነት ለፖሊስ ያላሳወቁ እንደሆነ ከሦስት እስከ አሥር ዓመት በሚደርስ ጽኑ እሥራት ሊያስቀጣዎት እንደሚችል የጸረ ሽብር ሕጉ አንቀጽ 35 ላይ ተደንግጎ ይገኛል፡፡

እንዲህ ዓይነት የማከራየት ዕድል ሳይገጥምዎ ተከራይ የሆኑ እንደሆነ ወይም አከራይ ዘመድ፣ ጓደኛ፣ ቤተሰብ ያለዎት እንደሆነ ይህንን የሕጉን ግዴታ በማሳወቅ የድርሻዎን መወጣትዎን አይርሱ! ወይም አከራይዎት ስለማንነትዎ በጠየቀ ጊዜ ወይም መታወቂያዎትን ኮፒ እንዲያደርጉ ሲጠይቆዎት መተባበርን አይዘንጉ መልእክታችን ነው፡፡

ውድ አንባቢያን ለዛሬ ያዘጋጀንላችሁን ጥንቅር በዚሁ አበቃን በቀጣይ በሌላ ፕሮግራም እስክንገናኝ መልካም ጊዜን ተመኘን፡፡መረጃውን ያገኘነው ከአቢሲኒያ ለው ድህረ-ገጽ ላይ ነው ሰላም፡፡
https://telegram.me/lawsocieties