አለሕግAleHig ️
16.2K subscribers
2.85K photos
25 videos
1.86K files
3.57K links
ከጠበቃና የሕግ አማካሪ
አማራጭ የሕግ እውቀትና አገልግሎት
Alternative legal enlightenment & Service
Website: alehig.com
https://linktr.ee/alehig
WhatsApp👉 #+251920666595
Telegram👉 @MikiasMelak
የሕግ ምክርና ድጋፍ፣ የተለያዩ ህጎች፤ አዋጅ፣ ደንብ፣ መመሪያ፣ #የሕግ_መረጃ
Download Telegram
ፍርድ ቤትን መድፈር ምን ማለት ነው?
ፍርድ ቤት መድፈርን የተመለከተው የኢትዮጵያ ሕግ በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕጉና በወንጀል ሕጉ ላይ ተደንግጎ እናገኘዋለን፡፡ የፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕጉ ዘጠነኛ መጽሐፍ ከአንቀጽ 480-482 ፍርድ ቤትን ለማስከበር ፍርድ ቤቶች የተሰጣቸውን ሥልጣን በዝርዝር ያስቀምጣል፡፡ በዚህ ሕግ መሠረት የማንኛውም ፍርድ ቤት ችሎት ዳኛ ፍርድ ቤቱንና የዳኝነት ሥራ አካሄድ ሥነ ሥርዓትን ለማስከበር ማናቸውንም አስፈላጊ መስሎ የታየውን ዕርምጃ እንዲወስድ ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡ ይህንን ለማስፈጸም ለፍርድ ቤቱ ችሎት ክብር ወይም ለዳኝነቱ ሥነ ሥርዓት መልካም አመራር ተቃራኒ የሆነ ጠባይ የሚያሳየውን ማንኛውንም ተከራካሪ ወገን ወይም ጠበቃ ወይም በችሎት ውስጥ የሚገኘውን ማንኛውንም ሰው ተቃራኒ ተግባር በሚሠራበት ጊዜ በያዘው መዝገብ ላይ የገንዘብ መቀጮ ሊወስንበት ይችላል፡፡ 
የፍትሐብሔር ሥነ-ሥርዓት ሕጉ አንቀጽ 481 እና የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 449 ለፍርድ ቤት መድፈር ዝርዝር ትርጉም የሚሰጡ ሲሆን፣ የአፈጻጸሙ ሥርዓትና ቅጣቶቹንም ደንግገዋል፡፡
የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 449 ላይ የተደነገገውን ስንመለከት ፍርድ ቤትን መድፈር በፍርድ ቤት ውስጥ ወይም ከፍርድ ቤት ውጪ ሊሆን የሚችል ሲሆን፤ ማንኛውም ሰው በፍርድ ቤት ምርመራ በሚደረግበት ወይም የፍርድ ሥራ በሚከናወንበት ጊዜ ፍርድ ቤቱን ወይም የዳኝነት ሥራ በማከናወን ላይ ያለውን ዳኛ በማናቸውም መንገድ ከሰደበ፣ ካወከ ወይም በነዚሁ ላይ ካፌዘ ወይም ከዛተ ወይም የፍርድ ቤቱን ሥራ በማናቸውም ሌላ መንገድ ካወከ፤ ወይም ደግሞ ፍርድ ቤቶች አከራካሪ የሆነ ቦታን ለመመልከት በአካል ከፍርድ ቤት ውጭ ሥራቸውን ሲያከናውኑ፣ በተዘዋዋሪ ችሎት ወይም ከያዙት መዝገብ ጋር በተያያዘ ከፍርድ ቤቱ ውጭ የተፈጸሙ ድርጊቶች በሙሉ የፍርድ ቤቱን ሥራ የሚያውኩ ከሆነ በፍርድ ቤት መድፈር ሊያስጠይቁ ይችላሉ፡፡
ድርጊቱ የተፈጸመው በችሎት ውስጥ ከሆነ ከአንድ ዓመት በማይበልጥ ቀላል እሥራት ወይም ከሶስት ሺህ ብር በማይበልጥ መቀጮ ይቀጣል፡፡ ለዚህ አይነቱ ጥፋት ፍርድ ቤቱ ቀጠሮ ሳያደርግ ወዲያውኑ በጥፋተኛው ላይ ቅጣት ሊወስን ይችላል፡፡
ወንጀሉ የተፈፀመው ከችሎት ውጭ ሆኖ ዳኛው ሥራውን እያከናወነ ባለበት ጊዜ ከሆነ፣ ቅጣቱ ከስድስት ወር የማይበልጥ ቀላል እሥራት ወይም ከአንድ ሺህ ብር የማይበልጥ መቀጮ ይሆናል፡፡
ሌላው ሊዘነጋ የማይገባው ቁምነገር ወንጀሉ የተፈጸመው በችሎት ወይም በማናቸውም ቦታ የዳኝነት ሥርዓት በሚካሄድበት ጊዜ ሆኖ በኃይል ወይም በማስገደድ ከሆነ፤ አግባብ ያለው ድንጋጌ /አንቀጽ 441/ በተደራቢነት ተፈጻሚ ይሆናል፡፡ ይህም ማለት ማንም ሰው አንድ የመንግሥት ሠራተኛ የሥራ ግዴታው የሆነውን ተግባር እንዳያከናውን በዛቻ፣ በማስገደድ ወይም በኃይል ድርጊት ካሰናከለ ወይም ይህን ግዴታውን እንዲያከናውን ወይም ማድረግ የሌለበትን እንዲያደርግ ካስገደደ ወይም የመንግሥት ሠራተኛን ወይም በስራው የሚረዳውን ሰው የደበደበ ወይም የኃይል ወይም የማስገደድ ድርጊት ወይም ማናቸውንም ሌላ የማስገደድ ድርጊት ከፈፀመ
ከሶስት ዓመት በማይበልጥ ቀላል እሥራት ወይም ከአምስት ሺህ ብር በማይበልጥ መቀጮ እንደሚቀጣ ተደንግጓል። እንደጥፋቱ ከባድነት መጠንና እንደ ተበዳዩም የሥራ ደረጃ ተበዳዩ በጦር መሣሪያ ወይም በሌላ መሣሪያ አማካይነት ተዝቶበት፣ ተገድዶ ወይም ተደብድቦ ከሆነ፤ ቅጣቱ ከአምስት ዓመት የማይበልጥ ጽኑ እሥራት ይሆናል፡፡
የእጅ እልፊቱ ወይም የኃይል ተግባሩ በተበዳዩ ላይ የአካል ጉዳት ወይም የጤንነት ጉድለት ካስከተለ፤ በተጨማሪነት በሌሎች ድንጋጌዎች ይታያል።
የሕጉ ዓላማ
በአብዛኛው ፍርድ ቤት መድፈር ዳኞች ለራሳቸው የግል ጥቅም ሲሉ ግለሰቦችን የሚቀጡ እንደሆነ ማሰብ በኅብረተሰቡ የተለመደ ነው፡፡ ሆኖም ዳኛው በግለሰብ ማንነቱ ላይ ብቻ የተቃጣን ድርጊት እንደማንኛውም ሰው ክስ አቅርቦ ሊጠይቀው የሚገባ እንጂ ከዳኛው ጋር የተያያዘ ተግባር ሁሉ ፍርድ ቤትን መድፈር ላይሆን ይችላል፡፡ ፍርድ ቤትን መድፈር በሕግ የተካተተበት ዓላማ የፍርድ ቤቱን ክብር ለመጠበቅ፣ የፍትሕ ሥርዓቱን ሕልውና ለመጠበቅ እንዲሁም ኅብረተሰቡ በዳኝነት አካሉ (በፍርድ ቤት) ላይ ያለውን መተማመን ለመጠበቅ ታስቦ ነው፡፡ የዳኝነት አካሉ ከሕግ አውጪውና ከሕግ አስፈጻሚው ጋር በፖለቲካ፣ በሕዝብ ገንዘብ አስተዳደርና በወታደራዊ አመራር እንደማይወዳደር ግልጽ ነው፡፡ ለፍርድ ቤት ህልውና መሠረት በሕዝብ መታመን ሲሆን ሥራውን በአግባቡ እንዲያከናውን ሕዝቡ እገዛ ያደርግለታል፡፡ በዚህ መነሻነት ፍርድ ቤቱ በኅብረተሰቡ ውስጥ ያለውን መተማመን የሚቀንስ ተግባር በሙሉ በሕግ ሊቀጣ ይገባል፡፡ ፍርድ ቤትን የመድፈር ድርጊቶች በዚህ ሥር የሚወድቁ ናቸው።
ምንጭ (Abisinia law.com)፣ የኢፌድሪ የወንጀል ህግ እና የፍትሃብሄር ስነ-ስርአት ህግ
ለሌሎች ህግ-ነክ መረጃዎች (የሀመር ወረዳ ፍትህ ጽ/ቤት) የሚለውን የቴሌግራም ገጻችንን ይቀላቀሉ…..።
የሐመር ወረዳ ፍትህ ጽ/ቤት
የህ/ጥ/ማ/ማ/ዋና ስራ ሂደት አቃቤ ህግ ህ/መ
https://t.me/lawsocieties
🟩 @lawsocieties
🟨 @lawsocieties
🟥 @lawsocieties