የ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ጽሑፎች በPDF እና በድምጽ
2.15K subscribers
51 photos
2 videos
26 files
54 links
እዚህ ቻናል ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እምነት የሚያንጸባርቁ ጽሑፎች ይለቀቃሉ
Download Telegram
የ"አባታችን ሆይ" ጸሎት አድምታ ትርጓሜ

ሐዋሪያት ወደ ጌታችን ቀርበው የምንጸልየውን ጸሎት አስተምረን አሉት። ጌታችንም "እናንተስ ስትጸልዩ የሰማይ አባታችን በሉኝ" በማለት ማንም ቢሆን ሲቆምና ሲቀመጥ ሲተኛና ሲነሣ ዘወትር ሊጸልየው የሚችለውን አጭር ጸሎት አስተማረ። ማቴዎስ 6÷9-14
ይኽም ጸሎት እንደ አባቶቻችን አስተምህሮ አድምታ ትርጓሜው አጠር ባለ መልኩ እንደሚከተለው ቀርቧል።

አባታችን ሆይ :-
ጌታችን ከግብርናተ ዲያብሎስ /ከዲያብሎስ ባርነት/ ነፃ እንዳወጣን: አጥተነው የነበረውን ልጅነት እንዳገኘን ሲያጠይቅ አቡነ /አባታችን/ በሉኝ አለ። ጌታ ሎሌውን መምህር ደቀመዝሙሩን ምን ቢወደው ያበላዋል ያጠጣዋል የልቡናውን ምስጢር ያጫውተዋል እንጂ ርስቱን አያወርሰውም። ርስቱን የሚያወርሰው ለልጁ ነው። እርሱ ግን ጌታችን እና አምላካችን ሲሆን የማታልፍ ርስት መንግሥተ ሰማያትን የሚያወርሰን ስለሆነ 'አቡነ' በሉኝ አለ። አባት ለወለደው ልጁ እዲራራ የሚራራልን ስለሆነ አቡነ በሉኝ አለ።

በሰማያት የምትኖር :-
እንዲህ ማለቱ ራሱን ከምድራዊ አባት ሲለይ ነው። ምድራዊ አባት ሲወልድ በግዙፍ ሲያሳድግ በግዙፍ ነው። ኋላም ሓላፊ ርስቱን ያወርሳል። እርሱ ግን ሲወልደን በረቂቅ ሲያሳድገን በረቂቅ ነው። ኋላም የማታልፍ ርስቱን መንግሥተ ሰማይን ያወርሰናል። በተጨማሪም ጌታ በሁሉ ምሉዕ ሲሆን ስለ ልዕልናው በሰማይ የምትኖር ይባላል። 1ኛጴጥ.1÷8-10 ራዕይ 21÷2-6።

ስምህ ይቀደስ:-
ይኽም "ስሜ መሐሪና ይቅር ባይ ነው።" ያልኸው ይጽናልን መላእክት ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ ብለው ስምህን አመስግነው ቅድስናህን ተሳትፈው እንዲኖሩ እኛም ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ ብለን አመሰገንህ ቅድስናህን ተሳትፈን እንድንኖር አድርገን በሉ ሲለን ነው። ኢሳያስ 6÷3 ራዕይ 4÷8።

መንግሥትህ ትምጣ:-
መንግሥተ ሰማይ ትምጣልን ልጅነትን ትሰጠን በሉ ሲል ነው። እንዲህም ማለቱ መንግሥተ ሰማይ ከወዲያ ወዲህ የምትመጣ ከወዲህም ወዲያ የምትሄድ ሆና ሳይሆን ትገለጽልን በሉ ማለቱ ነው። ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ፈሪሳውያን ቀርበው " የእግዚአብሔር መንግሥት መቼ ትመጣለች? " ብለው በጠየቁ ጊዜ "የእግዚአብሔር መንግሥት በመጠባበቅ አትመጣም ከዚህ አለች ከዚያ የለችም አትባልም የእግዚአብሔር መንግሥት እንሆ በመካከላችሁ ናት" ብሏቸዋል። ሉቃስ 10÷20-21።

ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነ እንዲሁ በምድር ትሁን :-
መላእክት ከሰማይ ሲያመሰግኑህ ፈቃድህ እንደ ሆነ እኛም በምድር ያለን ደቂቅ አዳም እናመስግንህ ዘንድ ፈቃድህ ይሁን። ኋላ ሞተን ተነሥተን እናመስግንህ ዘንድ ፈቃድህ ይሁን በሉ ሲል ነው። እንዲሁም አቤቱ ፈቃደ መዓትህን ትተህ ፈቃደ ምሕረትህን አድርግልን ብላችሁ ብትለምኑኝ አደርግላችኃለሁ ሲልም ነው።

የዕለት እንጀራችንን ስጠን ዛሬ :-
በዚህ ዓለም ሳለን ለዕለት የሚሆነንን ምግብ ስጠን በሉ ሲል ነው። በሰማይ ያሉ መላእክት ስብሐተ እግዚአብሔር ተመግበው / በሰማይ አመስግነውህ ያው ምስጋናቸው ምግብ ሆኗቸው/ እንዲኖሩ እኛም በምድር እህል ምግባችንን አትንሣን ብላችሁ ብትለምኑኝ አልነሣችሁም ሲል ነው።

በደላችንን ይቅር በለን የበደሉንን ይቅር እንደምንል:-
ማረን ይቅር በለን ኀጢአታችንን አስተስርይልን በደላችንን ደምስስልን መተላለፋችንን ሁሉ ይቅር በለን ይቅርታን እናገኝ ዘንድ እኛም የበደሉንን ሁሉ ይቅር እንላለን ሲል ነው። ለዚህም ነው ጌታ "ለሰዎች ኃጢአታቸውን ይቅር ብትሉ የሰማይ አባታችሁ ደግሞ ይቅር ይላችኋል ለሰዎች ግን ኃጢአታቸውን ይቅር ባትሉ አባታችሁም ኃጢአታችሁን ይቅር አይላችሁም" ብሏል። ማቴዎስ 6÷13-15። እንዲሁም "አበሳ" የዓመት ነው: " ጌጋዬ " / በደል / የዕለት ነው። አበሳ የዓመት ያለውም ነፍስ መግደል ቋንጃ መቁረጥ ቤት መስበርና ይኸንን የመሳሰለው ሁሉ ነው። ይኸን ያደረገም ጠላቱን ሲርበው ቢያበላ ሲጠማው ቢያጠጣው ሲታረዝ ቢያለብሰው በደለኛ ሲክሰው ዋስ ጠበቃ ቢሆነው ንስሐ ቢገባ ስለክፉ ሥራው ቢያዝን ቢጸጸት ቢያለቅስ ይድናል እንጂ ያለዚያስ አይድንም። ፊያታዊ ዘየማን ሲድን ፊያታዊ ዘጸጋም አለመዳኑ ንስሐ ባለመግባቱ ነው። ጌጋየ ዕለት ያለው ደግሞ ሰው ሆኖ በተለያየ ምክንያት መጣላት መጋጨት አይቀርምና ቂም በቀል ሳይዙ ዕለቱን ስለ እግዚአብሔር ይቅር መባባል ነው። ለዚህም ነው ሐዋርያው "በቁጣችሁ ፀሐይ አይግባ ለዲያብሎስም ፈንታ አትስጡት" ያለው። ኤፌሶን 4÷27

አቤቱ ወደ ፈተና አታግባን :-
ከክፉ አድነን ወደ ኀጢአት ወደ ክህደት ወደ መከራ ወደ ገሃነም አታግባን ከዚህ ሁሉ አድነን እንጂ በሉኝ ሲል ነው።

መንግሥትህ ያንተ ናትና:-
መንግሥተ ሰማያት ያንተ ገንዘብ ናትና በሉኝ ሲል ነው።

ኃይል ምስጋናም ለዘላለሙ:-
ከሃሊነት ጌትነት ለዘላለሙ ገንዘብህ ናትና አሜን በእውነት በሉኝ ሲል ነው። የእግዚአብሔር ኃይል የባሕርይ በመሆኑም ነው ጻድቁ ኢዮብ "ሁሉን ታደርግ ዘንድ ቻይ እንደሆንህ አሳብህም ይከለከል ዘንድ እንደማይችል አወቅሁ" በማለት የገለጸው ኢዮብ 42÷2

#ማጠቃለያ፡-
በዚህ የጸሎት ክፍል ውስጥ ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከ 81(ሰማንያ አሀዱ) መጽሐፍት የተገኙ አምስት ቁም ነገሮችን አስተምሯል እነሱም :-
1. ሃይማኖት
2. ተስፋ
3. ፍቅር
4. ትሕትና
5. ጸሎት ናቸው።

#በዘሪሁን_እሸቱ
Send this to your telegram friends
┈┈┈┈••●◉❖◉●••┈┈┈
@ethiopianorthodoxbooks
@ethiopianorthodoxbooks
@ethiopianorthodoxbooks
┈┈┈┈••●◉❖◉●••┈┈┈
To join our channel click the one in blue

ተዋሕዶ ለዘላለም ትኑር