ET Securities
644 subscribers
572 photos
7 videos
26 files
287 links
At Et securities our aim is in creating condusive space concerning capital markets and financial markets so as to enable learning and awareness creation to the society.

Support us https://t.me/boost/Etstocks

https://www.youtube.com/@etstocks
Download Telegram
#StockMarket

(የኢትዮጵያን ምጣኔ ሀብታዊ ጉዳዮችን በቅርበት በሚከታተሉት አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ በአንድ ወቅት ለቢቢሲ ድረገፅ ከሰጡት ቃለምልልስ የተወሰደ)

ስቶክ ገበያ ምንድነው ?

ለስቶክ ማርኬት ‘ የድርሻ ገበያ ’ የሚል አቻ የአማርኛ ትርጉም ልንሰጠው እንችላለን።

ኩባንያዎች የኩባንያውን የባለቤትነት ድርሻ ለገበያ ያቀርባሉ።

ሰዎች ይህን ድርሻ ከገዙ በኋላ ኩባንያው ትርፋማ በሆነ መጠን ያላቸውን ድርሻ መልሰው በመሸጥ ወይም ከትርፍ ክፍፍል ትርፋማ የሚያደርግ አሠራር ነው።

ስቶክ ማርኬት ለኢትዮጵያ ምን ይዞ ይመጣል ?

የስቶክ ገበያ በዋናነኝነት ለኢትዮጵያ የሚከተሉትን ጥቅሞች ይዞ ይመጣል።

1. የካፒታል ገበያ

በርካታ የአገር ውስጥ ባንክ እንዲሁም ኢንሹራንሶች ሲመሠረቱ እና ከምሥረታቸውም በኋላ የአክሲዮን ድርሻዎችን ሲሸጡ ቆይረዋል።

የስቶክ ገበያን ከዚህ የተለየ የሚያደርገው ፤ ይፋዊ በሆነ መልኩ ተደራጅቶ ቁጥጥር እየተገደረገበት በግልጽ መገበያየት ማስቻሉ ነው።

የኢትዮጵያን ሴኪዩሪቲስ ኤክስቼንጅ እውን ሲሆን ፤ ባንኮች እና ኢንሹራንሶች ሲቋቋሙም ሆነ ማስፋፋት ሲፈልጉ አክሲዮን ለመሸጥ ይከተሉት የነበረውን ረዥም መንገድ ያሳጥርላቸዋል።

እነዚህ ኩባንያዎች ሲቋቋሙ ስቶክ ኤክስቼንጅ ስላልነበረ በጣም ረዥም ሂደት በማለፍ ለእያንዳንዱ ሰው እየዞሩ ነው ሼር የሚሸጡት።

ይህ ረዥም ጊዜ እና ገንዘብ ይወስዳል። አዋጭም አይደለም።

የኢትዮጵያን ሴኪዩሪቲስ ኤክስቼንጅ አንዱ ጥቅም አዲስ ለመሚሠረቱም ሆነ ለነባር ኩባንያዎች የካፒታል ገበያን መፍጠሩ ነው።

ካፒታል ማሰባሰብ ለሚፈልጉ ስቶክ ገበያ መልካም አማራጭ ነው።

ጥሩ ሐሳብ ኖሯቸው የካፒታል እጥረት ላለባቸው ሰዎች ይጠቅማል።

ዛሬ ላይ ከባንክ ብድር ማግኘትም ቀላል አይለደም። ለዘመድ ወይም ለጓደኛ ሼር የመሸጥ ሂደት ቀላል አይደለም። ስቶክ ማርኬት አዲስ ለሆኑም ይሁን መስፋፋት ለሚፈልጉ ኩባንያዎች የካፒታል ገበያን ይፈጥራል።

2. ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል

የስቶክ ገበያ ፣ ፍትሐዊ እና ተመጣጣኝ በሆነ ሁኔታ ሀብት ማከፋፈል የሚችል ሥርዓት ነው።

በአሁኑ ጊዜ ግዙፍ መንግሥታዊ ኩባንያዎች ወደ ግሉ ዘርፍ እየተሸጋገሩ ነው።

እነዚህ ከመንግሥት ወደ ግሉ የሚዘዋወሩት ግዙፍ ኩባንያዎችን ሲገዙ የቆዩት ጥቂት ግለሰቦች እና ኮርፖሬሽኖች ናቸው። ስቶክ ማርኬት ሲመጣ ግን መንግሥት የሕዝብን ሀብት ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ማከፋፈል ይችላል።

ስቶክ ማርኬት ላይ 1 ሼር በአምስትም፣ በአሥርም ዶላር ሲሸጥ ሁሉም የየአቅሙን በመግዛት ኢትዮጵያ ያካበተችውን ሀብት ማከፋፈል ይቻላል።

እነዚህ ወደ ግሉ ዘርፍ የሚዘዋወሩ ኩባንያዎች ወደ ስቶክ ገበያው ሲገቡ፣ ሁሉም የአቅሙን ያህል ባለቤት ይሆናል። ይህም የሀብት ክፍፍልን ያመጣል።

3. ቁጠባ እና የኢንቨስትመንት አማራጭን ማስፋት

የቁጠባ ባህልን ከፍ ያደርጋል። ሰዎች በአሁኑ ጊዜ ኪሳራ አያስከትልም ብለው በሚያስቡት ዘርፍ ላይ ብቻ መዋዕለ ንዋያቸውን እያፈሰሱ ይገኛሉ።

ገንዘብ ያላቸው ሰዎች #የቤቶች_ልማት ላይ ብቻ ትኩረት ሲያደርጉ ይታያል። የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ደግሞ ተጎድቷል። ይህም ኢንቨስት የሚደረግባቸው ዘርፎችን ውስን በማድረግ የቁጠባ አለመመጣጠን ይፈጥራል።

ስቶክ ማርኬቱ ግን ውጤታማ በሆነ መንገድ ካፒታል በሁሉም ዘርፎች ላይ ማሰራጨት ያስችላል።

4. ግልጽነት

የድርሻ ገበያዎችን በቀላሉ፣ ግልጸኝነት በሰፈነበት መልኩ መግዛት እና መሸጥ ማስቻሉ ነው።

ምን ያህል ሼር በምን ያህል ዋጋ ለገበያ እንደቀረበ ግልጽ ነው።

ሰዎች ስልካቸው ላይ በሚጭኑት መተግበሪያ በቀላሉ የገበያ ድርሻዎችን መግዛት እና የገዙትንም መሸጥ ይችላሉ።

የባንክ ባለ አክሲዮኖች ዓመት ጠብቀው ትርፍ ከመከፋፈል ውጪ በቀላሉ ያላቸውን አክሲዮን መሸጥ አይቻላቸውም።

ስቶክ ማርኬት ሲሆን በቀላሉ አክሲዮን የመሸጥ ዕድል ይዘረጋል።

በስቶክ ገበያ ትርፍና ኪሳራ እንዴት ያጋጥማል ?

ይህንን ጥያቄ ከመመለሳችን በፊት ስቶክ ገበያ ምንድን ነው ? እንዴትስ መሸጥ እና መለወጥ ይቻላል ? የሚለውን እንመልከት።

ስቶክ ገበያን በቀላል ቋንቋ ለመረዳት የምጣሄ ሀብት ባለሙያዎች አዘወትረው የሚጠቀሙትን ቀላል ምሳሌ እንውሰድ። 'ሀ'፣ 'ለ' እና 'ሐ' የሚባሉ ሦስት ምናባዊ የሞባይል ስልክ አምራች ኩባንያዎችን አሉ አንበል።

እርስዎ 6 ዶላር አውጥተው ከእያንዳንዱ ኩባንያ የሁለት ዶላር የገበያ ድርሻ ይገዛሉ።

'ሀ' ለገበያ ያቀረበው ሞባይል ስልክ ባትሪ እየፈነዳ ሰዎችን ለጉዳት እየዳረገ መሆኑን የሚያመለክት ሪፖርት መውጣት ይጀምራል።

የ'ለ' ኩባንያ የሆነው ምርት ደግሞ ባትሪ በፍጥነት እያለቀ ከተጠቃሚዎች ቅሬታ ይደርሰዋል።

የ'ሐ' ምርት የሆነው ሞባይል ስልክ ግን በአግባቡ ይሠራል።

ይህ በገበያ ላይ ያጋጠመው ክስተት በሦስቱ ኩባንያዎች ስቶክ ገበያ ዋጋ ላይ ለውጥ ያመጣል። የአንድ ኩባንያ ምርት ጥራት ሲወርድ የዚያ ኩባንያ ፈላጊዎች ይቀንሳሉ።

በተቀራኒው አንድ ኩባንያ ትርፍማ የሚያደርገውን ውሳኔ ወስኖ ትርፍ ሲያጋብስ፣ የትርፉ ተቋዳሽ መሆን የሚሹ ሰዎች ቁጥር ከፍ ይላል።

በዚህ መሠረት ባትሪው እየፈነዳ ሰዎችን ለአደጋ እያጋለጠ ያለው የሞባይል ኩባንያ ድርሻ በከፍተኛ መጠን ሊወርድ ይችላል።

በሁለት ዶላር የገዙትን ድርሻ መልሰው መሸጥ ቢፈልጉ ከግማሸ ባነሰ ዋጋ እንኳን የሚገዛዎትን ላያገኙ ይችላሉ።

ይህ ሞባይል አምራች ኩባንያ ሲከስር እርስዎም የኩባንያው ባለድርሻ እንደመሆንዎ ኪሳራ ያጋጥምዎታል።

ስለዚህ በኩባንያ 'ሀ' ላይ ያደረጉት ኢንቨስትመንት ኪሳራን ያስከትላል።

የ 'ሐ' ምርት የሆነው ስልክ ግን በገበያ ተፈላጊነቱ ሲጨምር የኩባንያው ዋጋም ከፍ ይላል።

ምናልባት በሁለት ዶላር የገዙትን የኩባንያውን ድርሻ፣ አሁን ላይ በ4 ዶላር ሸጠው ትርፍ ሊያገኙ ይችላሉ።

@etstocks